ሕዝቅኤል 43:7-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህ የዙፋኔ መቀመጫ የእግሬም ጫማ ማሳረፊያ ነው፤ በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም የምኖርበትም ስፍራ ነው። የእስራኤል ቤትም ሆኑ ነገሥታታቸው በአመንዝራነታቸውና በማምለኪያ ኰረብታቸው ላይ በሚያመልኳቸው፣ ሕይወት በሌላቸው በነገሥታታቸው ጣዖታት ከእንግዲህ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም።

8. በእኔና በጣዖታቱ መካከል ግንብ ብቻ ሲቀር፣ መድረኮቻቸውን ከመድረኬ አጠገብ፣ መቃኖቻቸውን ከመቃኖቼ አጠገብ በማድረግ፣ በአስጸያፊ ድርጊታቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለዚህ በቍጣዬ አጠፋኋቸው።

9. ከእንግዲህ አመንዝራነታቸውንና ሕይወት የሌላቸውን የንጉሦቻቸውን ጣዖታት ከእኔ ዘንድ ያርቁ፤ እኔም በመካከላቸው ለዘላለም እኖራለሁ።

10. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ኀጢአታቸው ያፍሩ ዘንድ፣ ለእስራኤል ሕዝብ ቤተ መቅደሱን አሳያቸው፤ ንድፉንም ያስተውሉ፤

11. ስላደረጉት ነገር ሁሉ ኀፍረት የሚሰማቸው ከሆነ፣ የቤተ መቅደሱን ንድፍ እንዲያውቁት አድርግ፤ ይኸውም አሠራሩን፣ መውጫና መግቢያውን፣ አጠቃላይ ንድፉን፣ ሥርዐቱንና ሕጉን ሁሉ ነው። ንድፉንና ሥርዐቱን እንዲጠብቁና እንዲከተሉ እነዚህን ሁሉ እነርሱ ባሉበት ጻፋቸው።

12. “የቤተ መቅደሱ ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ጫፍ አካባቢ ያለው ስፍራ ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። የቤተ መቅደሱም ሕግ ይኸው ነው።

13. “የመሠዊያው ልክ በረጅም ክንድ ይህ ነው፤ ይኸውም ክንድ ከስንዝር ማለት ነው፤ ቦዩ አንድ ክንድ ጥልቀት፣ አንድ ክንድ ወርድ ያለው ሲሆን፣ ዙሪያው አንድ ስንዝር ጠርዝ አለው፤ የመሠዊያውም ከፍታ ይህ ነው፤

14. ከቦዩ መሠረት አንሥቶ እስከታችኛው ዕርከን ድረስ ሁለት ክንድ ቁመት፣ ሁለት ክንድ ወርድ ያለው ሲሆን፣ ከትንሹ ዕርከን አንሥቶ እስከ ትልቁ ዕርከን ድረስ ደግሞ አራት ክንድ ቁመት፣ አንድ ክንድ ወርድ አለው።

15. የመሠዊያው ምድጃ ከፍታው አራት ክንድ ሲሆን፣ ከምድጃው ወጣ ወጣ ያሉ አራት ቀንዶች አሉ።

16. የመሠዊያው ምድጃ እኩል በእኩል ሲሆን፣ ርዝመቱ ዐሥራ ሁለት ክንድ፣ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነው።

17. ላይኛው ዕርከንም እንዲሁ እኩል በእኩል ሆኖ ዐሥራ አራት ክንድ ርዝመትና ዐሥራ አራት ክንድ ወርድ አለው፤ ግማሽ ክንድ ጠርዝና ዙሪያውን በሙሉ አንድ ክንድ የሆነ ቦይ ነበረው። የመሠዊያው ደረጃዎችም በምሥራቅ ትይዩ ናቸው።”

18. ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ መሠዊያው ተሠርቶ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚሠዋበትና በመሠዊያው ላይ ደም በሚረጭበት ጊዜ ሥርዐቶቹ እነዚህ ናቸው፤”

19. በፊቴ ቀርበው ለሚያገለግሉኝ ካህናት፣ ለሌዋውያኑ ለሳዶቅ ቤተ ሰብ የኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ስጥ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 43