1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን በማጎግ ምድር በሚገኘው፣ በሞሳሕና በቶቤል ዋና አለቃ በጎግ ላይ አድርግ፤ በእርሱ ላይ ትንቢት ተናገር፤
3. እንዲህም በል፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሞሳሕና የቶቤል ዋና አለቃ ጎግ ሆይ፤ ተነሥቼብሃለሁ።
4. ወደ ኋላ እመልስሃለሁ፤ መንጋጋህ ውስጥ መንጠቆ አስገብቼ ከመላው ሰራዊትህ ጋር፣ ፈረሶችህን፣ ፈረሰኞችህን ከነሙሉ ትጥቃቸው፣ ትልቅና ትንሽ ሰይፍ የያዙትን ሁሉ፣ ሰይፋቸውንም የወለወሉትን ሁሉ አስወጣለሁ።
5. ጋሻ የያዙና የራስ ቍር የደፉት ሁሉ፣ ፋርስ፣ ኢትዮጵያና ፉጥ ከእነርሱ ጋር ይሆናሉ።
6. ደግሞም ጎሜርን ከወታደሮቹ ጋር፣ ራቅ ካለው ሰሜንም የቴርጋማን ቤት ከወታደሮቹ ሁሉ ጋር ብዙ ሕዝቦችን ከአንተ ጋር አስወጣለሁ።”
7. “ ‘አንተና በዙሪያህ የተሰበሰቡት ሁሉ ተነሡ፤ ተዘጋጁ፤ አንተም መሪያቸው ሁን።
8. ከብዙ ቀን በኋላ ለጦርነት ትጠራለህ። በኋለኛው ዘመንም ከጦርነት ያገገመችውን፣ሕዝቧ ከአያሌ አሕዛብ መካከል ወጥቶ የተሰበሰበውን፣ ለብዙ ጊዜ ባድማ በነበረው በእስራኤል ተራሮች ላይ የሰፈረውን ወገን ትወራለህ። ከሕዝቦች መካከል ወጥተው፣ አሁን ሁሉም በሰላም ይኖራሉ።