1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን በማጎግ ምድር በሚገኘው፣ በሞሳሕና በቶቤል ዋና አለቃ በጎግ ላይ አድርግ፤ በእርሱ ላይ ትንቢት ተናገር፤
3. እንዲህም በል፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሞሳሕና የቶቤል ዋና አለቃ ጎግ ሆይ፤ ተነሥቼብሃለሁ።
4. ወደ ኋላ እመልስሃለሁ፤ መንጋጋህ ውስጥ መንጠቆ አስገብቼ ከመላው ሰራዊትህ ጋር፣ ፈረሶችህን፣ ፈረሰኞችህን ከነሙሉ ትጥቃቸው፣ ትልቅና ትንሽ ሰይፍ የያዙትን ሁሉ፣ ሰይፋቸውንም የወለወሉትን ሁሉ አስወጣለሁ።
5. ጋሻ የያዙና የራስ ቍር የደፉት ሁሉ፣ ፋርስ፣ ኢትዮጵያና ፉጥ ከእነርሱ ጋር ይሆናሉ።