ሕዝቅኤል 36:21-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. የእስራኤል ቤት በሄዱበት በአሕዛብ መካከል ሁሉ፣ ስላረከሱት ቅዱስ ስሜ ገዶኛል።

22. “ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ይህን ሁሉ የማደርገው ስለ እናንተ ብዬ ሳይሆን፣ በየሄዳችሁባቸው አሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ስል ነው።

23. በአሕዛብ መካከል የረከሰውን፣ እናንተ በእነርሱ ዘንድ ያረከሳችሁትን፣ የታላቁን ስሜን ቅድስና አሳያለሁ፤ ከዚያም ዐይኖቻቸው እያዩ፣ በእናንተ አማካይነት ራሴን ቅዱስ አድርጌ ስገልጥ፣ አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

24. “ ‘ከአሕዛብ መካከል አስወጣችኋለሁ፤ ከየአገሩ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራችሁም መልሼ አመጣችኋለሁ።

25. ንጹሕ ውሃ እረጫችኋለሁ፤ እናንተም ንጹሕ ትሆናላችሁ፤ ከርኵሰታችሁ ሁሉና ከጣዖታቶቻችሁ ሁሉ አነጻችኋለሁ።

26. አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ የድንጋይ ልባችሁን ከእናንተ አስወግዳለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ።

27. መንፈሴን በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ ሥርዐቴን እንድትከተሉና ሕጌን በጥንቃቄ እንድትጠብቁ አደርጋለሁ።

ሕዝቅኤል 36