ሕዝቅኤል 36:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. መላው የእስራኤል ቤት እንኳ ሳትቀሩ፣ የሰዎችን ቍጥር በእናንተ ላይ አበዛለሁ። ከተሞች የሰው መኖሪያ ይሆናሉ፤ የፈረሱት እንደ ገና ይሠራሉ።

11. በእናንተ ላይ የሰዎችንና የእንስሳትን ቍጥር እጨምራለሁ፤ ፍሬያማ ይሆናሉ፤ ቍጥራቸውም ይበዛል። እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ ሰዎች በውስጣችሁ እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ካለፈው የበለጠ አበለጽጋችኋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

12. ሰዎችን፣ ሕዝቤን እስራኤልን በእናንተ ላይ እንዲመላለሱ አደርጋለሁ፤ ይወርሷችኋል፤ እናንተም ርስታቸው ትሆናላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ አልባ አታደርጓቸውም።

13. “ ‘ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቡ እናንተን፣ ‘ሰዎችን ቦጫጭቀው ይበላሉ፤ ሕዝብንም ልጅ አልባ ያደርጋሉ’ ስላሏችሁ፣

14. ከእንግዲህ ሰው አትበሉም፤ ሕዝቡንም ልጅ አልባ አታደርጉትም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

15. ከእንግዲህ የሕዝቦችን ዘለፋ እንድትሰሙ አላደርግም፤ በሰዎችም ስድብ አትሠቃዩም፤ ከእንግዲህ ለሕዝባችሁ መሰናክል አትሆኑም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

16. እንደ ገና የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

17. የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ሕዝብ በገዛ ምድራቸው ይኖሩ በነበረበት ጊዜ በሥራቸውና በአኗኗራቸው አረከሷት፤ ጠባያቸውም በፊቴ፣ ሴት በወር አበባዋ ወቅት እንደምትረክሰው ዐይነት ነበር።

18. ስለዚህ በምድሪቱ ላይ ደም ስላፈሰሱና በጣዖታቶቻቸው ስላረከሷት፣ መዓቴን አፈሰ ስሁባቸው።

19. በአሕዛብ መካከል በተንኋቸው፤ እነርሱም በየአገሩ ተበታተኑ፤ እንደ ጠባያቸውና እንደ ሥራቸው መጠን ፈረድሁባቸው።

20. በአሕዛብ መካከል በሄዱበት ሁሉ ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለ እነርሱ፣ ‘እነዚህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ናቸው፤ ዳሩ ግን የእርሱን ምድር ትተው እንዲሄዱ ተገደዱ’ ተብሎአልና።

21. የእስራኤል ቤት በሄዱበት በአሕዛብ መካከል ሁሉ፣ ስላረከሱት ቅዱስ ስሜ ገዶኛል።

ሕዝቅኤል 36