1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ራሳቸውን ብቻ ለሚንከባከቡ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች መንጋውን ማሰማራት አልነበረባቸውምን?
3. ጮማውን ትበላላችሁ፤ ከጠጒሩ የተሠራውን ሱፍ ትለብሳላችሁ፤ የሰባውን ዐረዳችሁ፤ ነገር ግን መንጋውን አትንከባ ከቡትም።
4. ደካማውን አላበረታችሁትም፤ በሽተኛውን አልፈወሳችሁትም፤ የተጐዳውንም አልጠገናችሁትም። የባዘኑትን አልመለሳችሁም፤ የጠፉትንም አልፈለጋችሁም፤ በግፍና በጭካኔ ገዛችኋቸው።
5. ስለዚህ እረኛ የለምና ተበተኑ፤ በመበተናቸውም ለአራዊቱ ሁሉ መብል ሆኑ።
6. በጎቼ በየተራራው ሁሉና በየኰረብታው ላይ ተንከራተቱ። በምድር ሁሉ ተበተኑ፤ የፈለጋቸውም፤ የፈቀዳቸውም የለም።
7. “ ‘ስለዚህ እናንት እረኞች፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤
8. በሕያውነቴ እምላለሁ፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እረኞቼ መንጋዬን ስላልፈለጉ፣ ከመንጋዬም ይልቅ ራሳቸውን ስለተንከባከቡ፣ መንጋዬ እረኛ አጥቶ ለንጥቂያ ተዳርጎአል፤ ለአራዊትም ሁሉ መብል ሆኖአል።