8. በሰማይ የሚያበሩትን ብርሃናት ሁሉ፣በአንተ ላይ አጨልማለሁ፤በምድርህ ላይ ጨለማን አመጣለሁ፤ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
9. በማታውቀው ምድር፣በሕዝቦች መካከል ያንተን ጥፋት ሳመጣ፣የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ።
10. ሕዝቦች በአንተ ላይ ከደረሰው የተነሣ እንዲደነግጡ አደርጋለሁ፤ሰይፌን በፊታቸው ስነቀንቅ፣በአንተ ላይ ከደረሰው ሁኔታ የተነሣ ንጉሦቻቸው ይንቀጠቀጣሉ።አንተ በምትወድቅበት ቀን፣እያንዳንዳቸው ስለ ራሳቸው ሕይወት በመፍራት፣በየቅጽበቱ ይርበደበዳሉ።
11. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤“ ‘የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ፣በአንተ ላይ ይመጣል።
12. ከሕዝቦች ሁሉ እጅግ ጨካኝ በሆኑት፣በኀያላን ሰዎች ሰይፍ፣ያከማቸኸው ሰራዊት እንዲወድቅ አደርጋለሁ፤የግብፅን ኵራት ያንኰታኵታሉ፤የሰራዊቷም ብዛት ይጠፋል፤
13. ብዙ ውሃ ባለበት አጠገብ ያለውን፣የከብት መንጋዋን አጠፋለሁ፤ከእንግዲህ የሰው እግር አይረጋግጠውም፤የከብትም ኮቴ አያደፈርሰውም።
14. ከዚያም ውሆቿን አጠራለሁ፤ወንዞቿም እንደ ዘይት እንዲፈሱ አደርጋለሁ፤ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15. ግብፅን ባድማ ሳደርጋት፣ምድሪቱም ያላትን ሁሉ ያጣች ስትሆን፣በዚያም የሚኖሩትን ሁሉ ስመታ፣ያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።”
16. “ስለ እርሷ የሚያወርዱት ሙሾ ይህ ነው፤ የሕዝቦች ሴት ልጆች ያዜሙታል፤ ስለ ግብፅና ስለ ብዙ ሰራዊቷ ሁሉ ሙሾ ያወርዳሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
17. በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ ከወሩም በዐሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
18. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ብዙው የግብፅ ሰራዊት አልቅስ፤ እርሷንና የኀያላንን ሕዝቦች ሴት ልጆች ወደ ጒድጓድ ከሚወርዱት ጋር ከምድር በታች አውርዳቸው።
19. እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንተ ከሌሎች የተለያችሁ ናችሁን? ውረዱ፤ ባልተገረዙትም መካከል ተጋደሙ።’
20. እነርሱም በሰይፍ በተገደሉት መካከል ይወድቃሉ፤ ሰይፉ ተመዟል፤ ከብዙ ሰራዊቷ ሁሉ ጋር ትጐተት።
21. በመቃብርም ውስጥ ኀያላኑ መሪዎች ስለ ግብፅና ስለ ተባባሪዎቿ፣ ‘ወደ ታች ወርደዋል፤ በሰይፍ ከተገደሉትና ካልተገረዙትም ጋር በአንድ ላይ ተጋድመዋል’ ይላሉ።
22. “አሦር ከመላው ሰራዊቷ ጋር በዚያ ትገኛለች፤ በሰይፍ በወደቁባትና በታረዱባት ሰዎች ሁሉ መቃብር ተከባለች።
23. መቃብራቸው በጥልቁ ጒድጓድ ውስጥ ነው፤ ሰራዊቷም በመቃብሯ ዙሪያ ተረፍርፏል። በሕያዋን ምድር ሽብርን የነዙ ሁሉ ታርደዋል፤ በሰይፍም ወድቀዋል።
24. “ኤላም በዚያ አለች፤ ሰራዊቷም ሁሉ በመቃብሯ ዙሪያ አለ፤ ሁሉም ታርደዋል፤ በሰይፍ ወድቀዋል። በሕያዋን ምድር ሽብር የነዙ ሁሉ ሳይገረዙ ከምድር በታች ወርደዋል፤ ወደ ጒድጓድ ከወረዱት ጋር ዕፍረታቸውን ተሸክመዋል፤
25. በመቃብሯ ዙሪያ ካለው መላው ሰራዊቷ ጋር፣ በታረዱት መካከል መኝታ ተዘጋጅቶላታል። ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፤ ሽብራቸው በሕያዋን ምድር ስለ ተነዛ፣ ወደ ጒድጓድ ከሚወርዱት ጋር ዕፍረታቸውን ይሸከማሉ፤ በታረዱትም መካከል ይጋደማሉ።