15. ግብፅን ባድማ ሳደርጋት፣ምድሪቱም ያላትን ሁሉ ያጣች ስትሆን፣በዚያም የሚኖሩትን ሁሉ ስመታ፣ያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።”
16. “ስለ እርሷ የሚያወርዱት ሙሾ ይህ ነው፤ የሕዝቦች ሴት ልጆች ያዜሙታል፤ ስለ ግብፅና ስለ ብዙ ሰራዊቷ ሁሉ ሙሾ ያወርዳሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
17. በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ ከወሩም በዐሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
18. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ብዙው የግብፅ ሰራዊት አልቅስ፤ እርሷንና የኀያላንን ሕዝቦች ሴት ልጆች ወደ ጒድጓድ ከሚወርዱት ጋር ከምድር በታች አውርዳቸው።
19. እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንተ ከሌሎች የተለያችሁ ናችሁን? ውረዱ፤ ባልተገረዙትም መካከል ተጋደሙ።’