11. የአራድና የሔሌክ ሰዎች፣ቅጥርሽን በየአቅጣጫው ጠበቁ፤የገማድ ሰዎችም፣ በምሽግሽ ውስጥ ነበሩ።ጋሻቸውንም በቅጥርሽ ዙሪያ ሰቀሉ፤ውበትሽንም ፍጹም አደረጉ።
12. “ ‘ከሀብትሽ ብዛት የተነሣ፣ ተርሴስ ከአንቺ ጋር የንግድ ልውውጥ ታደርግ ነበር፤ ብርና ብረት፣ ቈርቈሮና እርሳስ አምጥታ ሸቀጥሽን ትለውጥ ነበር።
13. “ ‘ያዋን፣ ቶቤልና ሞሳሕ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር፤ ባሪያዎችንና የናስ ዕቃዎችን በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።
14. “ ‘የቤት ቴርጋማ ሰዎችም መጋዣዎችን፣ የጦር ፈረሶችንና በቅሎዎችን በሸቀጥሽ ለወጡ።
15. “ ‘የድዳን ሰዎች ከአንቺ ጋር ተገበያዩ፤ብዙ የጠረፍ አገሮችም የንግድ ደንበኞችሽ ነበሩ፤ በዝኆን ጥርስና በዞጲ ሸቀጥሽን ይገዙ ነበር።
16. “ ‘ምርትሽ ብዙ እንደ መሆኑ፣ ሶርያ ከአንቺ ጋር ትገበያይ ነበር፤ ሸቀጥሽንም በበሉር፣ በሐምራዊ ጨርቅ፣ በወርቀ ዘቦ፣ በጥሩ በፍታ፣ በዛጐልና በቀይ ዕንቍ ይለውጡ ነበር።
17. “ ‘ይሁዳና እስራኤል እንኳ ከአንቺ ጋር ተገበያይተዋል፤ የሚኒትን ስንዴ፣ ጣፋጭ ቂጣ፣ ማር፣ ዘይትና በለሳን በማምጣት በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።
18. “ ‘ከሀብት ከንብረትሽ ብዛት የተነሣ፣ ደማስቆ የኬልቦንን የወይን ጠጅና፣ የዛሐርን የበግ ጠጒር በማቅረብ ከአንቺ ጋር ተገበያ ይታለች።
19. “ ‘ዌንዳንና ያዋን ከኦሴል መጥተው ከአንቺ ጋር የንግድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር፤ ቀልጦ የተሠራ ብረትን፣ ብርጒድንና ቀረፋን በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።
20. “ ‘ድዳን ግላስ በማቅረብ ከአንቺ ጋር ትነግድ ነበር።
21. “ ‘የዐረብና የቄዳር መሳፍንት ሁሉ ደምበኞችሽ ነበሩ፤ ጠቦትና አውራ በግ፣ ፍየልም አምጥተው ከአንቺ ጋር ይገበያዩ ነበር።
22. “ ‘የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች ከአንቺ ጋር ይገበያዩ ነበር፤ ምርጥ የሆነውን የሽቱ ቅመም ዐይነት ሁሉ፣ የከበረ ድንጋይና ወርቅ በማቅረብ በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።
23. “ ‘ካራን፣ ካኔ፣ ዔደን፣ የሳባ ነጋዴዎች፣ አሦርና ኪልማድ ከአንቺ ጋር የንግድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር።