ሕዝቅኤል 24:15-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

16. “የሰው ልጅ ሆይ፤ የዐይንህ ማረፊያ የሆነውን ነገር በመቅሠፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተ ግን ዋይታ አታሰማ፤ አታልቅስ፤ እንባህንም አታፍስስ፤

17. ድምፅህን ዝቅ አድርገህ በሐዘን አንጐራጒር እንጂ ለሞተው አታልቅስ። ጥምጥምህን ከራስህ አታውርድ፤ ጫማህንም አታውልቅ፤ አፍህ ድረስ አትሸፋፈን፤ የዕዝን እንጀራም አትብላ።”

18. እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፤ ሚስቴም ማታውኑ ሞተች፤ በማግሥቱም ጠዋት እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ።

19. ሕዝቡም፣ “ይህን ስታደርግ ለእኛ የምታስተላልፈው መልእክት ምን እንደሆነ አትነግረንምን?” አሉኝ።

20. እኔም እንዲህ አልኋቸው፤ “የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

21. ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የኀይላችሁን ትምክሕት፣ የዐይናችሁ ማረፊያና የልባችሁ ደስታ የሆነውን መቅደሴን አረክሳለሁ። ትታችኋቸው የሄዳችሁ ወንድና ሴት ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።

22. እኔ እንዳደረግሁም ታደርጋላችሁ፤ አፋችሁ ድረስ አትሸፋፈኑም፤ የዕዝን እንጀራም አትበሉም፤

23. ጥምጥማችሁን ከራሳችሁ አታወርዱም፤ ጫማችሁንም አታወልቁም። በኀጢአታችሁ ትመነምናላችሁ፤ እርስ በርስ ታቃስታላችሁ እንጂ ሐዘን አትቀመጡም፤ አታለቅሱምም።

24. ሕዝቅኤል ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ እንዳደረገው ታደርጋላችሁ፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”

25. “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፤ ኀይላቸውን፣ ደስታቸውንና፣ ክብራቸውን፣ የዐይናቸው ማረፊያና የልባቸው ደስታ የሆኑትን ወንድና ሴት ልጆቻቸውን ጭምር በምወስድባቸው ቀን፣

26. በዚያን ቀን፣ ያመለጠ ሰው ይህን ወሬ ሊነግርህ ወደ አንተ ይመጣል፤

27. በዚያን ቀን አፍህ ተከፍቶ ከእርሱ ጋር ትነጋገራለህ፤ ከዚያም በኋላ እንደ ድዳ አትሆንም፤ ምልክትም ትሆናቸዋለህ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።”

ሕዝቅኤል 24