1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ከአንድ እናት የተወለዱ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩ፤
3. ገና በወጣትነታቸው ዘማውያት በመሆን በግብፅ ሳሉ አመነዘሩ፤ በዚያችም ምድር አጐጠጐጤአቸው ተዳበሰ፤ የድንግልናቸውም ጒያ በእጅ ተሻሸ።
4. የታላቂቱ ስም ኦሖላ፣ የእኅቷም ኦሖሊባ ነበር፤ ሁለቱም የእኔ ሆኑ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ወለዱ። ስማቸውም፣ ኦሖላ ሰማርያ ናት፤ ኦሖሊባም ኢየሩሳሌም።
5. “ኦሖላ የእኔ ሆና ሳለ በእኔ ላይ አመነዘረች፤ ጦረኞች ከሆኑት ጎረቤቶቿ ከአሦራውያን ውሽሞቿ ጋር ሴሰነች፤
6. እነርሱም ሐምራዊ የለበሱ፣ ገዦችና አዛዦች፣ ሁሉም መልከ ቀና ጐበዛዝትና ፈጣን ፈረሰኞች ነበሩ።
7. እርሷ በዝሙት ራሷን ምርጥ ለሆኑት አሦራውያን ሁሉ አሳልፋ ሰጠች፤ አብረዋት ባመነዘሩት ሰዎች ጣዖት ሁሉ ረከሰች።