1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም አዙር፤ በመቅደሱ ላይ ቃል ተናገር፤ በእስራኤል ምድር ላይ ትንቢት ተንብይ፤
3. እንዲህም በል፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ሰይፌን ከሰገባው እመዛለሁ፤ ጻድቁንም፣ ክፉውንም ከአንተ ዘንድ አስወግዳለሁ።
4. ጻድቁንም ክፉውንም ስለማስወ ግድ ሰይፌ ከደቡብ ጀምሮ እስከ ሰሜን ባለው ሕዝብ ሁሉ ላይ ከሰገባው ይመዘዛል።
5. ሰይፌን ከሰገባው የመዘዝሁት እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ሕዝቡ ሁሉ ያውቃል፤ እርሱም ወደ ሰገባው አይመለስም።’
6. “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ አቃስት፤ በተሰበረ ልብና በመረረ ሐዘን አቃስት፤
7. እነርሱም፣ ‘ለምን ታቃስታለህ?’ ቢሉህ፣ “ስለሚመጣው ክፉ ወሬ ነው፤ ልብ ሁሉ ይቀልጣል፤ እጅም ሁሉ ይዝላል፤ ነፍስ ሁሉ ይደክማል፤ ጒልበትም ሁሉ ውሃ ይሆናል’ በላቸው። እነሆ ይመጣል፤ ይፈጸማልም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”