ሕዝቅኤል 20:9-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ነገር ግን በመካከላቸው በኖሩባቸውና እስራኤልን ከግብፅ ምድር ለመታደግ ቃል ስገባ፣ በእነርሱ ዘንድ በተገለጥሁት በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ክብር ተቈጠብሁ።

10. ስለዚህ ከግብፅ አውጥቼ ወደ ምድረ በዳ አመጣኋቸው።

11. ሰው ቢጠብቀው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን ሰጠኋቸው፤ ሕጌንም አስታወቅኋቸው።

12. ደግሞም እኔ እግዚአብሔር እንደ ቀደስኋቸው ያውቁ ዘንድ፣ በእኔና በእነርሱ መካከልም ምልክት እንዲሆን ሰንበቴን ሰጠኋቸው።

13. “ ‘ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ዐመፀብኝ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሕጌንም ተላለፉ፤ ሰንበቴንም ፈጽሞ አረከሱ። እኔም መዓቴን ላፈስባቸው፣ በምድረ በዳም ላጠፋቸው ወስኜ ነበር።

14. ነገር ግን ከመካከላቸው ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ተቈጠብሁ።

15. ደግሞም ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈሰው፣ ወደ ሰጠኋቸውም ምድር እንደማላስገባቸው እጆቼን አንሥቼ በምድረ በዳ በፊታቸው ማልሁ፤

16. ምክንያቱም ሕጎቼን ተላልፈዋል፤ ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሰንበቴንም አርክሰዋል፤ ልባቸው ከጣዖቶቻቸው ጋር ተጣብቆአልና።

17. እኔ ግን በርኅራኄ ተመለከትኋቸው እንጂ አላጠፋኋቸውም፤ በምድረ በዳም አልፈጀኋቸውም።

18. ለልጆቻቸው በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፤ “የአባቶቻችሁን ሥርዐት አትከተሉ፤ ወጋቸውን አትጠብቁ፤ ራሳችሁንም በጣዖቶቻቸው አታርክሱ።

ሕዝቅኤል 20