ሕዝቅኤል 20:32-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

32. “ ‘እናንተም፣ “ለዕንጨትና ለድንጋይ እንደሚሰግዱ እንደ አሕዛብ፣ በዓለምም እንደሚኖረው ሕዝብ ሁሉ እንሁን” አላችሁ፤ ነገር ግን በልባችሁ ያሰባችሁት ከቶ አይሆንላችሁም።

33. በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ መዓትንም በማፍሰስ በላያችሁ እነግሣለሁ።

34. ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ፣ መዓትንም በማፍሰስ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች ሁሉ እሰበስባችኋለሁ።

35. ወደ አሕዛብ ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ፤ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ።

36. በግብፅ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ፣ ከእናንተም ጋር እፋረዳለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

37. ከበትሬ በታች አሳልፋችኋለሁ፤ ከቃል ኪዳኔም ጋር አጣብቃችኋለሁ።

38. በእኔ ላይ ያመፁትንና የበደሉኝን ከመካከላችሁ አስወግዳለሁ፤ ከሚኖሩበት አገር አወጣቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

39. “ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለ እናንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የማትሰሙኝ ከሆነ፣ እያንዳንዳችሁ ሂዱና ለጣዖታቶቻችሁ ስገዱ! ነገር ግን በቍርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን ከእንግዲህ አታረክሱም።

ሕዝቅኤል 20