24. ምክንያቱም ሥርዐቴን አቃለሉ፤ ሰንበቴን አረከሱ እንጂ ሕጌን አልጠበቁም፤ ዐይናቸውም ከአባቶቻቸው ጣዖታት ጋር ተጣብቆአል።
25. እኔም መልካም ላልሆነ ሥርዐትና በሕይወት ለማይኖሩበት ሕግ አሳልፌ ሰጠኋቸው፤
26. እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ እንዲያውቁ፣ አስደነግጣቸውም ዘንድ በእሳት በሚያቀርቡት የበኵር ልጅ መሥዋዕት እንዲረክሱ አደረግኋቸው።’
27. “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አባቶቻችሁ እኔን በመተው በዚህ ደግሞ አቃለሉኝ፤
28. ልሰጣቸው ወደማልሁላቸው ምድር ባስገባኋቸው ጊዜ፣ ከፍ ያለውን ኰረብታ ሁሉና የለመለመውን ዛፍ ሁሉ ተመለከቱ፤ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ፤ ቍርባናቸውን በማቅረብ ቍጣዬን አነሣሡ፤ መልካም መዐዛ ያለውን ዕጣናቸውን ዐጠኑ፤ የመጠጥ ቍርባናቸውንም አፈሰሱ።”
29. እኔም፣ ‘የምትሄዱበት ይህ ከፍታ ቦታ ምንድን ነው?” አልኋቸው።’ እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ይጠራል።
30. “ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አባቶቻችሁ እንዳደረጉት ራሳችሁን ታረክሳላችሁን? በረከሱ ምስሎቻቸው ምኞት ትቃጠላላችሁን?
31. ቍርባናችሁን በምታቀርቡበት ጊዜ ልጆቻችሁን ለእሳት በመዳረግ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ሁሉ እየረከሳችሁ ናችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ታዲያ የእኔን ሐሳብ እንድትጠይቁ ልፍቀድላች ሁን? በሕያውነቴ እምላለሁ እንድትጠይቁኝ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
32. “ ‘እናንተም፣ “ለዕንጨትና ለድንጋይ እንደሚሰግዱ እንደ አሕዛብ፣ በዓለምም እንደሚኖረው ሕዝብ ሁሉ እንሁን” አላችሁ፤ ነገር ግን በልባችሁ ያሰባችሁት ከቶ አይሆንላችሁም።
33. በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ መዓትንም በማፍሰስ በላያችሁ እነግሣለሁ።