ሕዝቅኤል 20:11-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ሰው ቢጠብቀው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን ሰጠኋቸው፤ ሕጌንም አስታወቅኋቸው።

12. ደግሞም እኔ እግዚአብሔር እንደ ቀደስኋቸው ያውቁ ዘንድ፣ በእኔና በእነርሱ መካከልም ምልክት እንዲሆን ሰንበቴን ሰጠኋቸው።

13. “ ‘ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ዐመፀብኝ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሕጌንም ተላለፉ፤ ሰንበቴንም ፈጽሞ አረከሱ። እኔም መዓቴን ላፈስባቸው፣ በምድረ በዳም ላጠፋቸው ወስኜ ነበር።

14. ነገር ግን ከመካከላቸው ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ተቈጠብሁ።

15. ደግሞም ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈሰው፣ ወደ ሰጠኋቸውም ምድር እንደማላስገባቸው እጆቼን አንሥቼ በምድረ በዳ በፊታቸው ማልሁ፤

16. ምክንያቱም ሕጎቼን ተላልፈዋል፤ ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሰንበቴንም አርክሰዋል፤ ልባቸው ከጣዖቶቻቸው ጋር ተጣብቆአልና።

17. እኔ ግን በርኅራኄ ተመለከትኋቸው እንጂ አላጠፋኋቸውም፤ በምድረ በዳም አልፈጀኋቸውም።

18. ለልጆቻቸው በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፤ “የአባቶቻችሁን ሥርዐት አትከተሉ፤ ወጋቸውን አትጠብቁ፤ ራሳችሁንም በጣዖቶቻቸው አታርክሱ።

19. እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ ሥርዐቴን ተከተሉ፤ ሕጌንም ለመጠበቅ ትጉ።

20. በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆን ዘንድ ሰንበቴን የተቀደሰ ቀን አድርጉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁም ታውቃላችሁ።’

21. “ ‘ልጆቻቸው ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልተከተሉም፤ ሕጌን ለመጠበቅ አልተጉም፤ ሰንበቴንም አረከሱ። እኔም በምድረ በዳ መዓቴን አፈስባቸዋለሁ፤ ቍጣዬንም አወርድባቸዋለሁ ብዬ ነበር።

22. ነገር ግን ከግብፅ ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ እጄን ሰበሰብሁ።

23. ደግሞም በአሕዛብ መካከል እንደምበትናቸውና ወደ ተለያዩ አገሮች እንደማፈልሳቸው በምድረ በዳ እጄን አንሥቼ በፊታቸው ማልሁ፤

24. ምክንያቱም ሥርዐቴን አቃለሉ፤ ሰንበቴን አረከሱ እንጂ ሕጌን አልጠበቁም፤ ዐይናቸውም ከአባቶቻቸው ጣዖታት ጋር ተጣብቆአል።

25. እኔም መልካም ላልሆነ ሥርዐትና በሕይወት ለማይኖሩበት ሕግ አሳልፌ ሰጠኋቸው፤

26. እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ እንዲያውቁ፣ አስደነግጣቸውም ዘንድ በእሳት በሚያቀርቡት የበኵር ልጅ መሥዋዕት እንዲረክሱ አደረግኋቸው።’

27. “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አባቶቻችሁ እኔን በመተው በዚህ ደግሞ አቃለሉኝ፤

ሕዝቅኤል 20