8. “ዳግመኛም በአጠገብሽ በማልፍበት ጊዜ ወደ አንቺ ተመለከትሁ፤ ለመፈቀርም እንደ ደረስሽ ባየሁ ጊዜ፣ የመጐናጸፊያዬን ዘርፍ በላይሽ ዘርግቼ ዕርቃንሽን ሸፈንሁ። ማልሁልሽ፤ ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ተጋባሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺም የእኔ ሆንሽ።
9. “በውሃ አጥቤ ከደም አጠራሁሽ፤ ዘይትም ቀባሁሽ።
10. ወርቀ ዘቦ አለበስሁሽ፤ ምርጥ ቈዳ ጫማም አደረግሁልሽ፤ ያማረ በፍታ አለበስሁሽ ውድ መደረቢያም አጐናጸፍሁሽ።
11. በጌጣጌጥ አንቈጠቈጥሁሽ፤ በእጅሽ አንባር፣ በዐንገትሽም ድሪ አጠለቅሁልሽ፤
12. በአፍንጫሽ ቀለበት፣ በጆሮሽ ጉትቻ፣ በራስሽም ላይ ውብ አክሊል አደረግሁልሽ፤
13. በወርቅና በብር አጌጥሽ፤ ልብስሽም ያማረ በፍታ፣ ሐርና ወርቀ ዘቦ ነበር፤ ምግብሽም የላመ ዱቄት፣ ማርና የወይራ ዘይት ነበር። እጅግ ውብ ሆንሽ፤ ንግሥት ለመሆንም በቃሽ።
14. እኔ ከሰጠሁሽ ሞገስ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም በመሆኑ ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ገነነ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15. “ ‘ነገር ግን በውበትሽ ተመካሽ፤ ዝናሽንም ለአመንዝራነት ተጠቀምሽበት፤ ከዐላፊ አግዳሚው ጋር ያለ ገደብ አመነዘርሽ ውበትሽም ለማንም ሆነ።
16. ከልብስሽ አንዳንዱን ወስደሽ የምታመነዝሪበትን መስገጃ ስፍራ አስጌጥሽበት፤ እንዲህ ዐይነት ነገር ከዚህ ቀደም አልታየም፤ ወደ ፊትም አይኖርም።
17. ከሰጠሁሽ ወርቄና ብሬ የተሠራውን ምርጥ ጌጣጌጥ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ አበጀሽ፤ ከእነርሱም ጋር ዝሙት ፈጸምሽ።