2. በመንፈሳዊ ነገር የተጉ ሰዎችም እስጢፋኖስን ቀበሩት፤ ደግሞም እጅግ አለቀሱለት።
3. ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ታጥቆ ተነሣ፤ ከቤት ወደ ቤት በመግባትም ወንዶችንና ሴቶችን ጐትቶ እያወጣ ወህኒ ቤት ያስገባቸው ነበር።
4. የተበተኑትም በሄዱበት ሁሉ ቃሉን ሰበኩ፤
5. ፊልጶስም ወደ አንዲት የሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው።
6. ብዙ ሕዝብም ፊልጶስ የተናገረውን ሲሰሙና ያደረገውንም ታምራዊ ምልክቶች ሲያዩ፣ አንድ ልብ ሆነው ያዳምጡት ነበር።
7. ርኵሳን መናፍስትም እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ወጡ፤ ብዙ ሽባዎችና አንካሶችም ተፈወሱ፤
8. ከዚህ የተነሣም በከተማዪቱ ታላቅ ደስታ ሆነ።