ሐዋርያት ሥራ 5:24-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. የቤተ መቅደሱ ጥበቃ ሹምና የካህናት አለቆችም ይህን በሰሙ ጊዜ በነገሩ ተገረሙ፤ ግራም ተጋቡ።

25. በዚህ ጊዜ አንድ ሰው መጥቶ፣ “እነሆ፤ እስር ቤት ያስገባችኋቸው ሰዎች በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቆመው ሕዝቡን እያስ ተማሩ ናቸው” አላቸው።

26. የጥበቃ ሹሙም ከወታደሮቹ ጋር ሄዶ፣ ይዞ አመጣቸው፤ ያመጧቸው ግን ሕዝቡ በድንጋይ እንዳይወግሯቸው ስለ ፈሩ በኀይል ሳያስገድዱ ነበር።

27. ሐዋርያትንም አምጥተው በሸንጎው ፊት አቆሟቸው፤ ሊቀ ካህናቱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤

28. “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ በጥብቅ አስጠንቅቀናችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ ደግሞም እኛን ለዚህ ሰው ደም ተጠያቂዎች ልታደርጉን ቈርጣችሁ ተነሣችሁ።”

29. ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያትም መልሰው እንዲህ አሉ፤ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!

30. እናንተ በዕንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን፣ የአባቶቻችን አምላክ ከሙታን አስነሣው፤

31. እርሱም ለእስራኤል ንስሓንና የኀጢአትን ስርየት ይሰጥ ዘንድ፣ እግዚአብሔር የሁሉ ራስና አዳኝ አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው።

32. እኛም ለእነዚህ ነገሮች ምስክር ነን፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።”

33. ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ክፉኛ ተቈጡ፤ ሊገድሏቸውም ፈለጉ።

34. ነገር ግን በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ አንድ የሕግ መምህር፣ እርሱም ገማልያል የሚሉት ፈሪሳዊ ተነሥቶ በሸንጎው መካከል ቆመና ሐዋርያትን ወደ ውጭ አውጥተው ለጥቂት ጊዜ እንዲያዩአቸው አዘዘ፤

35. ለሸንጎውም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ስላሰባችሁት ነገር በጥንቃቄ ልታጤኑ ይገባችኋል።

ሐዋርያት ሥራ 5