ሐዋርያት ሥራ 28:6-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ሰዎቹ ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል ወይም ድንገት ሞቶ ይወድቃል ብለው ይጠባበቁ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ጠብቀው ምንም የተለየ ነገር እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ፣ ሐሳባቸውን ለውጠው፣ “ይህስ አምላክ ነው” አሉ።

7. በዚያም ስፍራ አጠገብ የደሴቲቱ አለቃ የፑፕልዮስ ርስት የሆነ መሬት ነበረ፤ እርሱም በቤቱ ተቀብሎን ሦስት ቀን በቸርነት አስተናገደን።

8. የፑፕልዮስም አባት በትኵሳትና በተቅማጥ ሕመም ተይዞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ሊጠይቀው ገብቶ ከጸለየለት በኋላ፣ እጁን ጭኖ ፈወሰው።

9. ይህም በሆነ ጊዜ፣ በደሴቲቱ የነበሩ ሌሎች ሕመምተኞችም እየመጡ ተፈወሱ።

10. እኛንም በብዙ መንገድ አከበሩን፤ በመርከብም ለመሄድ በተዘጋጀን ጊዜ፣ የሚያስፈልገንን ሁሉ ጫኑልን።

11. ከሦስት ወር በኋላም፣ በደሴቲቱ ክረምቱን ቆሞ በሰነበተ በአንድ መርከብ ተነሥተን ጒዞ ጀመርን። ይህም መርከብ የእስክንድርያ ሲሆን፣ በላዩ ላይ የመንታ አማልክቱ የዲዮስቆሮስ አርማ ነበረበት።

12. ወደ ሰራኩስ ከተማ ገብተን ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጥን።

13. ከዚያም በመርከብ ተጒዘን ሬጊዩም ደረስን፤ በማግስቱም የደቡብ ነፋስ ስለ ተነሣ ፑቲዮሉስ የደረስነው በሚቀጥለው ቀን ነበር።

14. በዚያም ወንድሞችን አገኘን፤ እነርሱም ሰባት ቀን አብረናቸው እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሮም ሄድን።

15. በዚያ የነበሩ ወንድሞችም መምጣታችንን ስለ ሰሙ፣ እስከ አፍዩስ ፋሩስ፣ እንዲሁም ‘ሦስት ማደሪያ’ እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን ወጡ፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ተጽናናም።

16. ሮም በደረስን ጊዜም፣ ጳውሎስ ይጠብቀው ከነበረው ወታደር ጋር፣ ለብቻው በዚያ እንዲቈይ ተፈቀደለት።

17. ከሦስት ቀንም በኋላ፣ ጳውሎስ የአይሁድን መሪዎች በአንድነት ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፤ እኔ፣ ሕዝባችንን ወይም የአባቶቻችንን ሥርዐት የሚቃረን ምንም ሳላደርግ፣ በኢየሩሳሌም አስረው ለሮማውያን አሳልፈው ሰጥተውኛል።

18. እነርሱም መርምረው ለሞት የሚያበቃ በደል ስላላገኙብኝ፣ ሊፈቱኝ ፈልገው ነበር፤

19. አይሁድ በተቃወሙ ጊዜ ግን፣ ለቄሳር ይግባኝ ማለት ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስበት ምክንያት ኖሮኝ አይደለም።

20. እናንተንም ለማየትና ለማነጋገር የጠራኋችሁ በዚሁ ምክንያት ነው፤ በዚህ ሰንሰለት የታሰርሁትም ለእስራኤል በተሰጠው ተስፋ ምክንያት ነው።”

21. እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ስለ አንተ ከይሁዳ ምድር የተጻፈ አንድም ደብዳቤ አልደረሰንም፤ ከዚያ የመጡ ወንድሞችም ስለ አንተ ያቀረቡት ወይም የተናገሩት አንዳች መጥፎ ነገር የለም።

ሐዋርያት ሥራ 28