21. ስለዚህ እሺ አትበላቸው፤ ምክንያቱም ከመካከላቸው ከአርባ በላይ የሚሆኑት ሊገድሉት አድፍጠው እየጠበቁት ነው፤ ደግሞም እስኪገድሉት ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማምለዋል፤ አሁንም ተዘጋጅተው የአንተን መልስ እየተጠባበቁ ነው።”
22. የጦር አዛዡም፣ “ይህን ለእኔ የገለጥህልኝን ነገር ለማንም እንዳትናገር” ብሎ ጒልማሳውን አስጠንቅቆ አሰናበተው።
23. ከዚያም ከመቶ አለቆቹ ሁለቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ከምሽቱ ሦስት ሰዓት፣ ወደ ቂሳርያ የሚሄዱ ሁለት መቶ ወታደሮች፣ ሰባ ፈረሰኞችና ሁለት መቶ ባለ ጦር ጭፍራ አዘጋጁ፤
24. ደግሞም ጳውሎስ ተቀምጦበት ወደ አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ በደኅና የሚደርስበት ከብት ይዘጋጅ።”
25. ደብዳቤም ጻፈ፤ እንዲህ የሚል፦
26. ከቀላውዴዎስ ሉስዩስ፤ለክቡር አገረ ገዥ ለፊልክስ፤ሰላም ለአንተ ይሁን።
27. አይሁድ ይህን ሰው ይዘው ሊገድሉት ነበር፤ ነገር ግን የሮም ዜጋ መሆኑን ስላወቅሁ፣ ከወታደሮቼ ጋር ደርሼ አተረፍሁት።
28. ለምን ሊከሱት እንደ ፈለጉ ለማወቅም፣ ወደ ሸንጎአቸው አቀረብሁት።