ሐዋርያት ሥራ 23:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ጳውሎስም ወደ ሸንጎው ትኵር ብሎ በመመልከት፣ “ወንድሞች ሆይ፤ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በእግዚአብሔር ፊት በንጹሕ ሕሊና ተመላልሻለሁ” አለ።

2. በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ በጳውሎስ አጠገብ የቆሙትን ሰዎች አፉን እንዲመቱት አዘዘ።

3. ጳውሎስም፣ “አንተ በኖራ የተለሰንህ ግድግዳ! እግዚአብሔር ደግሞ አንተን ይመታሃል፤ በሕጉ መሠረት ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ፣ ያለ ሕግ ስላ ስመታኸኝ አንተ ራስህ ሕጉን ጥሰሃል” አለው።

4. ጳውሎስ አጠገብ ቆመው የነበሩትም፣ “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ደፍረህ ትሰድባለህን?” አሉት።

5. ጳውሎስም፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባለማወቄ ነው፤ ‘በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ አትናገር’ ተብሎ ተጽፎአልና” አላቸው።

6. ጳውሎስም ሕዝቡ፣ ከፊሎቹ ሰዱቃውያን፣ ከፊሎቹ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ስላወቀ፣ “ወንድሞቼ ሆይ፤ እኔ ከፈሪሳዊ የተወለድሁ ፈሪሳዊ ነኝ፣ ለፍርድ የቀረብሁትም የሙታንን ትንሣኤ ተስፋ በማድረጌ ነው” ሲል በሸንጎው ፊት ጮኸ።

7. ይህንንም በተናገረ ጊዜ፣ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጠብ ተነሣ፤ ሸንጎውም ለሁለት ተከፈለ።

8. ሰዱቃውያን የሙታን ትንሣኤ የለም፤ መላእክትም መናፍስትም የሉም የሚሉ ሲሆኑ፣ ፈሪሳውያን ግን በእነዚህ ሁሉ መኖር የሚያምኑ ነበሩ።

9. ታላቅ ሁከትም ሆነ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ የኦሪት ሕግ መምህራንም ተነሥተው፣ “በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይም መልአክ ተናግሮትስ እንደሆነ ምን ይታወቃል?” በማለት አጥብቀው ተከራከሩ።

10. ጠቡ ከማየሉ የተነሣም አዛዡ ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈራ፤ ስለዚህ ወታደሮቹ ወርደው ከመካከላቸው ነጥቀው ወደ ጦሩ ሰፈር እንዲያስገቡት አዘዘ።

11. በሚቀጥለውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ፣ “ጳውሎስ ሆይ፤ አይዞህ! በኢየሩሳሌም እንደ መሰከርህልኝ፣ በሮምም ደግሞ ልትመሰክርልኝ ይገባሃል” አለው።

12. በነጋም ጊዜ፣ አይሁድ ተሰብስበው በማሤር ጳውሎስን እስኪገድሉ ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማማሉ። በዚህ ሤራ

13. የተማማሉትም ከአርባ በላይ ነበሩ።

14. እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎች ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ጳውሎስን ሳንገድል እህል ላለመቅመስ ጽኑ መሐላ አድርገናል።

15. እንግዲህ እናንተ ከሸንጎው ጋር ሆናችሁ፣ ስለ ጒዳዩ ትክክለኛ የሆነ ተጨማሪ መረጃ ከእርሱ እንደምትፈልጉ አስመስላችሁ ጳውሎስን ወደ እናንተ እንዲሰደው የጦር አዛዡን ለምኑት፤ እኛም ገና ወደዚህ ሳይደርስ ልንገድለው ዝግጁ ነን።”

ሐዋርያት ሥራ 23