6. ነገር ግን በተቃወሙትና በሰደቡት ጊዜ ልብሱን አራግፎ፣ “ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ይሁን! እኔ ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” አላቸው።
7. ከዚያም ወጥቶ ቲቶስ ኢዮስጦስ ወደተባለ፣ እግዚአብሔርን ወደሚያመልክ ሰው ቤት ሄደ፤ የዚህም ሰው ቤት በምኵራቡ አጠገብ ነበር።
8. የምኵራብ አለቃ የነበረው ቀርስጶስ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፤ ጳውሎስ ሲናገር የሰሙ ብዙ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ተጠመቁ።
9. ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን እንዲህ አለው፤ “አትፍራ፤ ተናገር፣ ዝምም አትበል፤
10. እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ማንም በአንተ ላይ ተነሥቶ ሊጐዳህ አይችልም፤ በዚች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝና።”
11. ስለዚህ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማራቸው አንድ ዓመት ተኩል አብሮአቸው ተቀመጠ።
12. ጋልዮስ የአካይያ ገዥ በነበረበት ጊዜ አይሁድ ተባብረው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፤ ፍርድ ወንበር ፊት አቅርበውትም፣
13. “ይህ ሰው ሕጉ በማይፈቅደው መንገድ፣ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ እያሳሳታቸው ነው” አሉ።
14. ጳውሎስ ሊናገር ገና አፉን ሲከፍት፣ ጋልዮስ አይሁድን እንዲህ አላቸው፤ “የአይሁድ ሰዎች ሆይ፤ ያቀረባችሁት ጒዳይ ስለ ዐመፅ ወይም ስለ ከባድ ወንጀል ቢሆን ኖሮ ላዳምጣችሁ በተገባኝ ነበር፤
15. ነገር ግን ክርክራችሁ ስለ ቃላትና ስለ ስሞች እንዲሁም ስለ ሕጋችሁ በመሆኑ፣ እናንተው ጨርሱት፤ እኔ በእንዲህ ዐይነት ነገር ፈራጅ ለመሆን አልሻም።”
16. ስለዚህ ከፍርድ ወንበር ፊት አስወጣቸው።
17. በዚህ ጊዜ ሁሉም የምኵራቡን አለቃ፣ ሶስቴንስን ይዘው በፍርድ ቤቱ ፊት ደበደቡት፤ ጋልዮስ ግን ነገሩ ደንታም አልሰጠውም።
18. ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ብዙ ቀን በቆሮንቶስ ተቀመጠ፤ ከዚያም ወንድሞችን ተሰናብቶ ከጵርስቅላና ከአቂላ ጋር በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ። ስእለትም ስለ ነበረበት ክንክራኦስ በተባለ ቦታ ራሱን ተላጨ።
19. ኤፌሶን በደረሰ ጊዜም ጵርስቅላንና አቂላን እዚያው ተዋቸው፤ እርሱ ራሱ ግን ወደ ምኵራብ ገብቶ ከአይሁድ ጋር ይነጋገር ነበር።
20. ከእነርሱ ጋር እንዲሰነብት በጠየቁትም ጊዜ ፈቃደኛ አልሆነም፤