1. ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ተነሥቶ ወደ ቆሮንቶስ ሄደ።
2. በዚያም የጳንጦስ ተወላጅ የሆነውን፣ አቂላ የተባለውን አይሁዳዊ አገኘ፤ እርሱም አይሁድ ሁሉ ከሮም እንዲወጡ ቀላውዴዎስ ባዘዘው መሠረት ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር በቅርብ ጊዜ ከኢጣሊያ የመጣ ነበር። ጳውሎስም ሊያያቸው ወደ እነርሱ ሄደ፤
3. እርሱም እንደ እነርሱ ድንኳን ሰፊ ስለ ነበረ፣ ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ በተመሳሳይ ሥራ ላይ ተሰማራ።
4. በየሰንበቱም ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ጋር በምኵራብ ውስጥ እየተነጋገረ ሊያሳምናቸው ይጥር ነበር።
5. ሲላስና ጢሞቴዎስ ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስ በስብከት እየተጋ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ለአይሁድ ይመሰክር ነበር።
6. ነገር ግን በተቃወሙትና በሰደቡት ጊዜ ልብሱን አራግፎ፣ “ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ይሁን! እኔ ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” አላቸው።