5. አይሁድ ግን ስለቀኑ ወስላቶችን ከገበያ ቦታ አሰባሰቡ፤ ሕዝቡንም አነሣሥተው በከተማው ውስጥ ሁከት ፈጠሩ፤ ጳውሎስንና ሲላስንም አምጥተው ሕዝቡ ፊት ለማቅረብ ወደ ኢያሶን ቤት እየተጣደፉ ሄዱ፤
6. ነገር ግን ሊያገኟቸው አልቻሉም፤ ስለዚህ ኢያሶንንና ሌሎች ወንድሞችን በከተማው ባለ ሥልጣናት ፊት እየጐተቷቸው እንዲህ እያሉ ጮኹ፤ “እነዚህ ሰዎች ዓለሙን ሁሉ ሲያውኩ ቈይተው፣ አሁን ደግሞ ወደዚህ መጥተዋል፤
7. ኢያሶንም በቤቱ ተቀብሎአቸዋል፤ እነዚህም ሁሉ፣ ‘ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ’ በማለት የቄሳርን ሕግ የሚጥሱ ናቸው።”
8. ሕዝቡና የከተማውም ሹማምት ይህን በሰሙ ጊዜ ተሸበሩ፤
9. ከዚያም ኢያሶንንና ሌሎቹን በዋስ ለቀቋቸው።
10. ወንድሞችም ወዲያው ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፤ እነርሱም እዚያ በደረሱ ጊዜ፣ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ።
11. የቤርያ ሰዎች ከተሰሎንቄ ሰዎች ይልቅ አስተዋዮች ነበሩ፤ ምክንያቱም ነገሩ እንደዚህ ይሆንን እያሉ መጻሕፍትን በየዕለቱ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጒጒት ተቀብለዋል።
12. ስለዚህ ከእነርሱ ብዙዎቹ አመኑ፤ ደግሞም ከእነርሱ ጋር ቍጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ዕውቅ የግሪክ ሴቶችና ወንዶችም አመኑ።
13. በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድም፣ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል በቤርያ ጭምር መስበኩን ባወቁ ጊዜ፣ ሕዝቡን ለመቀስቀስና ለማነሣሣት ወደዚያ ደግሞ ሄዱ።
14. በዚህ ጊዜ ወንድሞች ጳውሎስን ቶሎ ብለው ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሰደዱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው ቀሩ።
15. ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም አቴና አደረሱት፤ ከዚያም ሲላስና ጢሞቴዎስ ወደ እርሱ በፍጥነት እንዲመጡ የሚል ትእዛዝ ተቀብለው ተመለሱ።