ሐዋርያት ሥራ 17:13-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድም፣ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል በቤርያ ጭምር መስበኩን ባወቁ ጊዜ፣ ሕዝቡን ለመቀስቀስና ለማነሣሣት ወደዚያ ደግሞ ሄዱ።

14. በዚህ ጊዜ ወንድሞች ጳውሎስን ቶሎ ብለው ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሰደዱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው ቀሩ።

15. ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም አቴና አደረሱት፤ ከዚያም ሲላስና ጢሞቴዎስ ወደ እርሱ በፍጥነት እንዲመጡ የሚል ትእዛዝ ተቀብለው ተመለሱ።

16. ጳውሎስ በአቴና ሆኖ ሲጠብቃቸው ሳለ፣ ከተማዪቱ በጣዖት የተሞላች መሆኗን በማየት መንፈሱ ተበሳጨበት።

17. ስለዚህ በምኵራብ ሆኖ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ግሪኮች ጋር፣ ደግሞም በገበያ ስፍራ ዕለት ዕለት ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይነጋገር ነበር።

18. ከኤፊቆሮስና ከኢስጦኢክ የፍልስፍና ወገን የሆኑትም ወደ እርሱ መጥተው ይከራከሩት ነበር። አንዳንዶቹ፣ “ይህ ለፍላፊ ምን ለማለት ይፈልጋል?” ይሉ ነበር፤ ሌሎች ደግሞ ስለ ኢየሱስና ስለ ትንሣኤው የምሥራች ሲሰብክ ሰምተው፣ “ስለ አዳዲስ ባዕዳን አማልክት የሚናገር ይመስላል” አሉ።

19. ይዘውም አርዮስፋጎስ ወደተባለው ስፍራ በመውሰድ እንዲህ አሉት፤ “አንተ የምታስተምረው ይህ አዲስ ትምህርት ምን እንደሆነ እንድናውቅ ትፈቅዳለህን?

20. ደግሞም በጆሮአችን የምታሰማን እንግዳ ነገር ስለ ሆነብን፣ ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን።”

21. የአቴና ሰዎች በሙሉ እንዲሁም በዚያ የሚኖሩ የውጭ ሰዎች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ስለ አዳዲስ ነገሮች በማውራትና በመስማት እንጂ በሌላ ጒዳይ አልነበረም።

22. ስለዚህ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፤ “የአቴና ሰዎች ሆይ፤ በማናቸውም ረገድ፣ በጣም ሃይማኖተኞች መሆናችሁን አያለሁ፤

23. እየተዘዋወርሁ ሳለሁ፣ የምታመልኳቸውን ነገሮች ስመለከት፣ ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሑፍ ያለበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁና፤ እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ።

24. “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነው፤ ስለዚህም እርሱ የሰው እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም።

25. እርሱ ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም።

26. የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን ፈጥሮ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ አደረገ፤ የዘመናቸውን ልክና የመኖሪያ ስፍራቸውንም ዳርቻ ወሰነላቸው።

27. ይኸውም ሰዎች እግዚአብሔርን ፈልገው ተመራምረው ምናልባት ያገኙት እንደሆነ ብሎ ነው፤ ይህም ቢሆን እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ሆኖ አይደለም፤

28. የምንኖረውና የምንንቀሳቀ ሰው፣ ያለነውም በእርሱ ነውና። ከራሳችሁ ባለቅኔዎችም አንዳንዶቹ እንዳሉት፣ ‘እኛም ደግሞ ልጆቹ ነን።’

29. “እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን፣ አምላክ በሰው ሙያና ጥበብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ ይመስላል ብለን ማሰብ አይገባንም።

30. ቀደም ሲል እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን አለማወቅ በትዕግሥት ዐልፎአል፤ አሁን ግን በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ ያዛል፤

31. በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኖአልና፤ እርሱንም ከሙታን በማስነሣቱ ለሰዎች ሁሉ ይህን አረጋግጦአል።”

32. እነርሱም ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ፣ አንዳንዶቹ አፌዙ፤ ሌሎች ግን፣ “ስለዚህ ጒዳይ ከአንተ ዳግመኛ ለመስማት እንፈልጋለን” አሉት።

33. በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጥቶ ሄደ፤

ሐዋርያት ሥራ 17