9. ጳውሎስም ሌሊት በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ፣ “ወደ መቄዶንያ ተሻግረህ ርዳን” ብሎ ሲለምነው አየ።
10. ጳውሎስ ይህን ራእይ ካየ በኋላ፣ እግዚአብሔር ወንጌልን እንድንሰብክላቸው ጠርቶናል ብለን በመወሰን ወዲያው ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ፈለግን።
11. ከጢሮአዳ በመርከብ ተነሥተን በቀጥታ ተጒዘን ወደ ሳሞትራቄ መጣን፤ በማግስቱም ጒዞአችንን ወደ ናጱሌ ቀጠልን፤
12. ከዚያም የሮማውያን ቅኝና የአካባቢው የመቄዶንያ ግዛት ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ፊልጵስዩስ ገባን፤ በዚያም አያሌ ቀን ተቀመጥን።
13. በሰንበት ቀንም፣ የጸሎት ስፍራ በመፈለግ፣ ከከተማዪቱ በር ወጥተን ወደ አንድ ወንዝ ወረድን፤ በዚያም ተቀምጠን ተሰብስበው ለነበሩት ሴቶች መናገር ጀመርን።
14. ከሚያዳምጡትም ሴቶች መካከል ልድያ የምትባል አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም እግዚአብሔርን የምታመልክና ከትያጥሮን ከተማ የመጣች የቀይ ሐር ነጋዴ ነበረች። ጌታም፣ ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል ትሰማ ዘንድ፣ ልቧን ከፈተላት።
15. እርሷና ቤተ ሰዎቿ ከተጠመቁ በኋላም፣ “በጌታ ማመኔን በርግጥ ከተረዳችሁልኝ ወደ ቤቴ መጥታችሁ ጥቂት ተቀመጡ” በማለት አጥብቃ ለመነችን።
16. አንድ ቀን ወደ ጸሎት ስፍራ ስንሄድ፣ በጥንቈላ መንፈስ ትንቢት የምትናገር አንዲት የቤት አገልጋይ አገኘችን፤ እርሷም በዚህ የጥንቈላ ሥራዋ ለአሳዳሪዎችዋ ብዙ ገንዘብ ታስገኝላቸው ነበር።
17. ይህችው አገልጋይ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፣ “እነዚህ ሰዎች የመዳንን መንገድ የሚነግሯችሁ፣ የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው!” በማለት ትጮኽ ነበር፤
18. ይህንም ብዙ ቀን ደጋገመችው፤ ጳውሎስ ግን በዚህ እጅግ በመታወኩ ዘወር ብሎ ያን መንፈስ፣ “ከእርሷ እንድትወጣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ” አለው፤ መንፈሱም በዚያው ቅጽበት ወጣላት።
19. አሳዳሪዎቿም የገንዘብ ማግኛ ተስፋቸው ወጥቶ መሄዱን በተረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው እየጐተቱ ባለ ሥልጣኖች ወዳሉበት ወደ ገበያ ቦታ አመጧቸው።
20. ገዦቹም ፊት አቅርበዋቸው እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ሳሉ፣ ከተማችንን አውከዋል፤
21. ደግሞም እኛ ሮማውያን መቀበል ወይም መፈጸም የማይገባንን ልማድ በሕዝቡ መካከል ይነዛሉ።”
22. ሕዝቡም ተባብረው በጳውሎስና በሲላስ ላይ ተነሡባቸው፤ ገዦቹም ልብሳቸው ተገፎ በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ።
23. ክፉኛ ከተደበደቡ በኋላም ወደ ወህኒ ቤት አስገቧቸው፤ የወህኒ ቤት ጠባቂውም ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት።