ሐዋርያት ሥራ 16:21-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ደግሞም እኛ ሮማውያን መቀበል ወይም መፈጸም የማይገባንን ልማድ በሕዝቡ መካከል ይነዛሉ።”

22. ሕዝቡም ተባብረው በጳውሎስና በሲላስ ላይ ተነሡባቸው፤ ገዦቹም ልብሳቸው ተገፎ በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ።

23. ክፉኛ ከተደበደቡ በኋላም ወደ ወህኒ ቤት አስገቧቸው፤ የወህኒ ቤት ጠባቂውም ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት።

24. እርሱም ይህን የመሰለ ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፣ ወደ ወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገብቶ እግራቸውን ከግንድ ጋር አጣብቆ አሰራቸው።

25. እኩለ ሌሊት አካባቢ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩና እየዘመሩ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ነበር፤ ሌሎቹ እስረኞችም ያዳምጧቸው ነበር።

26. ድንገትም የወህኒ ቤቱን መሠረት የሚያናውጥ ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ፤ ወዲያውም የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፈቱ፤ የሁሉም እስራት ተፈታ።

27. የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ከእንቅልፉ ነቅቶ የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፍተው ባየ ጊዜ፣ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ።

28. ጳውሎስ ግን ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እኛ ሁላችን እዚሁ ስላለን፣ በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርስ!” ብሎ ጮኸ።

29. የወህኒ ቤቱ ጠባቂም መብራት ለምኖ ወደ ውስጥ ዘሎ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ እግር ላይ ወደቀ፤

30. ይዞአቸው ከወጣ በኋላ፣ “እናንት ሰዎች፤ እድን ዘንድ ምን ላድርግ?” አላቸው።

31. እነርሱም፣ “በጌታ በኢየሱስ እመን፤ አንተም ቤተ ሰዎችህም ትድናላችሁ” አሉት።

32. ከዚያም ለእርሱና በቤቱ ላሉት ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ተናገሩ።

33. የወህኒ ቤት ጠባቂውም ሌሊት በዚያኑ ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፤ ወዲያውም እርሱና ቤተ ሰቡ ሁሉ ተጠመቁ።

34. የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ወደ ቤቱ ወስዶ ማእድ አቀረበላቸው፤ ከቤተ ሰቡም ሁሉ ጋር በእግዚአብሔር በማመኑ በደስታ ተሞላ።

35. ሲነጋም፣ ገዦቹ፣ “እነዚያን ሰዎች ፈተህ ልቀቃቸው” ብለው መኰንኖቻቸውን ላኩበት።

36. የወህኒ ቤት ጠባቂውም፣ “ገዦቹ እንድትፈቱ አዘዋል፤ ስለዚህ ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ” ብሎ ለጳውሎስ ነገረው።

37. ጳውሎስ ግን፣ “እኛ የሮም ዜጎች ሆነን ሳለን፣ በሕዝብ ፊት ያለ ፍርድ ደብድበው ወደ እስር ቤት ወረወሩን፤ ታዲያ አሁን በስውር ሊያስወጡን ይፈልጋሉ? ይህማ አይሆንም፤ እነርሱ ራሳቸው መጥተው ያስወጡን!” አላቸው።

38. መኰንኖቹም ይህንኑ ቃል ለገዦቹ ነገሯቸው፤ እነርሱም ጳውሎስና ሲላስ የሮም ዜጎች መሆናቸውን ሲሰሙ ደነገጡ፤

ሐዋርያት ሥራ 16