ሐዋርያት ሥራ 14:9-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ያደምጥ ነበር። ጳውሎስም ወደ እርሱ ትኵር ብሎ ተመለከተና ለመዳን እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ

10. በታላቅ ድምፅ፣ “ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም!” አለው፤ በዚህ ጊዜ ዘሎ ተነሣና መራመድ ጀመረ።

11. ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፣ በሊቃኦንያ ቋንቋ፣ “አማልክት በሰው ተመስለው ወደ እኛ ወርደዋል!” ብለው ጮኹ፤

12. በርናባስን ‘ድያ’ አሉት፤ ጳውሎስም ዋና ተናጋሪ ስለ ነበር ‘ሄርሜን’ አሉት።

13. ከከተማው ወጣ ብሎ የነበረው፣ የድያ ቤተ መቅደስ ካህንም ኰርማዎችንና የአበባ ጒንጒኖችን ወደ ከተማው መግቢያ አምጥቶ፣ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ፈለገ።

14. ሐዋርያቱ በርናባስና ጳውሎስ ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል ሮጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤

15. “እናንት ሰዎች፤ ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እኮ እንደ እናንተው ሰዎች ነን። እናንተም ደግሞ ከዚህ ከንቱ ነገር ርቃችሁ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር እንድትመለሱ ወንጌልን እንሰብክላችኋለን።

16. እርሱ ባለፉት ትውልዶች፣ ሕዝቦች ሁሉ በገዛ መንገዳቸው እንዲሄዱ ተዋቸው፤

17. ይሁን እንጂ ዝናብን ከሰማይ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠቱ፣ ደግሞም ልባችሁን በመብልና በደስታ በማርካቱ መልካምን በማድረግ ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።”

18. ይህን ሁሉ ተናግረው እንኳ፣ ሕዝቡ እንዳይሠዋላቸው ያስተዉት በብዙ ችግር ነበር።

ሐዋርያት ሥራ 14