ሉቃስ 5:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሕዝቡ ዙሪያውን እያጨናነቁት የሚያስተምረውን የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰሙ፣ ኢየሱስ በጌንሳሬጥ ሐይቅ አጠገብ ቆሞ ነበር፤

2. በዚህ ጊዜ ሁለት ጀልባዎች በሐይቁ ዳርቻ ቆመው አየ፤ ዓሣ አጥማጆቹ ግን ከጀልባዎቹ ወርደው መረባቸውን ያጥቡ ነበር።

3. ከጀልባዎቹም መካከል የስምዖን ወደ ነበረችው ገብቶ፣ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ ከዚያም ጀልባዋ ላይ ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ጀመር።

4. ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ስምዖንን፣ “ወደ ጥልቁ ውሃ ፈቀቅ በልና ዓሣ ለመያዝ መረባችሁን ጣሉ” አለው።

5. ስምዖንም መልሶ፣ “መምህር ሆይ፤ ሌሊቱን ሙሉ ስንደክም አድረን ምንም አልያዝንም፤ አንተ ካልህ ግን መረቦቹን እጥላለሁ” አለው።

6. እንደዚያም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረባቸውም ይበጣጠስ ጀመር።

7. በሌላ ጀልባ የነበሩት ባልንጀሮቻቸው መጥተው እንዲያግዟቸውም በምልክት ጠሯቸው፤ እነርሱም መጥተው ሁለቱን ጀልባዎች በዓሣ ሞሏቸው፣ ጀልባዎቹም መስመጥ ጀመሩ።

8. ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጒልበት ላይ ወድቆ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና ከእኔ ተለይ” አለው።

9. ይህንን ያለው እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት በያዙት ዓሣ ብዛት ስለ ተደነቁ ነው፤

10. ደግሞም የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩት የዘብዴዎስ ልጆች፣ ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ።ኢየሱስም ስምዖንን፣ “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” አለው።

ሉቃስ 5