19. እርሱም፣ “የሆነው ነገር ምንድን ነው?” አላቸው።እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት በተግባርና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፤
20. እርሱን የካህናት አለቆችና ገዦቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ ሰቀሉትም።
21. እኛ ግን እስራኤልን ይቤዣል ብለን ተስፋ ያደረግነው እርሱን ነበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው።
22. ደግሞም ከእኛው መካከል አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ እነርሱም ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤
23. ሥጋውንም ባጡ ጊዜ መጥተው እርሱ በሕይወት እንዳለ የነገሯቸውን መላእክት በራእይ እንዳዩ አወሩልን።
24. ከእኛም መካከል አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው፣ ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።”
25. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣
26. ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?”
27. ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው።
28. ወደሚሄዱበትም መንደር በተቃረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ አልፎ የሚሄድ መሰለ።
29. እነርሱ ግን፣ “ምሽት እየተቃረበ፣ ቀኑም እየመሸ ስለ ሆነ ከእኛ ጋር እደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለማደር ገባ።
30. አብሮአቸውም በማእድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው።
31. በዚህ ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተ፤ ዐወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ።
32. እነርሱም፣ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ።
33. በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤