40. ሌላኛው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ሲል ገሠጸው፤ “ተመሳሳይ ፍርድ እየተቀበልህ ሳለህ፣ ከቶ እግዚአብሔርን አትፈራምን?
41. እኛ ላደረግነው ነገር ቅጣት እየተቀበልን ስለ ሆነ፣ ተገቢ ፍርድ ላይ ነን፤ ይህ ሰው ግን አንዳች ክፉ ነገር አላደረገም።”
42. ደግሞም፣ “ኢየሱስ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” አለው።
43. ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው።
44. ጊዜው ስድስት ሰዓት ያህል ነበር፤ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፤
45. የፀሓይ ብርሃን ተከልክሎአልና። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ተቀዶ ለሁለት ተከፈለ።
46. ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ፣ “አባት ሆይ፤ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ” አለ፤ ይህንም ብሎ ሞተ።
47. የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ጻድቅ ነበር” ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነ።
48. ይህንኑ ለማየት በስፍራው ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችም ሁሉ የሆነውን ነገር በተመለከቱ ጊዜ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ።