ሉቃስ 22:59-68 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

59. አንድ ሰዓት ያህል ቈይቶም፣ ሌላ ሰው በርግጠኝነት፣ “ይህ ሰው ገሊላዊ ስለ ሆነ ያለ ጥርጥር ከእርሱ ጋር ነበረ” አለ።

60. ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ የምትለውን እኔ አላውቅም” አለ፤ ይህንም ተናግሮ ገና ሳይጨርስ ዶሮ ጮኸ።

61. ጌታም መለስ ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም፣ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ጌታ የተናገረው ቃል ትዝ አለው።

62. ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።

63. ኢየሱስን አስረው ይጠብቁት የነበሩት ሰዎችም ያፌዙበትና ይመቱት ጀመር፤

64. ዐይኑንም ሸፍነው፣ “እስቲ ትንቢት ተናገር፤ የመታህ ማነው? እያሉ ይጠይቁት ነበር።

65. ሌላም ብዙ የስድብ ቃል እየተናገሩ ያቃልሉት ነበር።

66. በነጋም ጊዜ፣ የሕዝብ ሽማግሌዎች፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም በሸንጎአቸው ፊት አቀረቡት።

67. እነርሱም፣ “አንተ ክርስቶስ ነህን? እስቲ ንገረን” አሉት።ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ብነግራችሁ አታምኑኝም፤

68. ብጠይቃችሁም አትመልሱም።

ሉቃስ 22