ሉቃስ 22:53-62 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

53. በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ እጃችሁን አላነሣችሁብኝም፤ ይህ ግን ጨለማ የነገሠበት ጊዜያችሁ ነው።”

54. ከዚህ በኋላ ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ አስገቡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተለው ነበር።

55. ሰዎቹ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳለ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ነበር።

56. አንዲት የቤት ሠራተኛም ጴጥሮስ እሳቱ አጠገብ ተቀምጦ አየችውና ትኵር ብላ በመመልከት፣ “ይህ ሰው ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ” አለች።

57. እርሱ ግን፣ “አንቺ ሴት፤ እኔ ዐላውቀውም” ብሎ ካደ።

58. ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንድ ሌላ ሰው አይቶት፣ “አንተም ደግሞ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አለው።ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ እኔ አይደለሁም” አለ።

59. አንድ ሰዓት ያህል ቈይቶም፣ ሌላ ሰው በርግጠኝነት፣ “ይህ ሰው ገሊላዊ ስለ ሆነ ያለ ጥርጥር ከእርሱ ጋር ነበረ” አለ።

60. ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ የምትለውን እኔ አላውቅም” አለ፤ ይህንም ተናግሮ ገና ሳይጨርስ ዶሮ ጮኸ።

61. ጌታም መለስ ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም፣ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ጌታ የተናገረው ቃል ትዝ አለው።

62. ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።

ሉቃስ 22