17. ስለ ስሜም በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
18. ነገር ግን ከራሳችሁ ጠጒር አንዷ እንኳ አትጠፋም፤
19. ጸንታችሁም በመቆም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ።
20. “ኢየሩሳሌም በጦር ሰራዊት ተከባ በምታዩበት ጊዜ፣ ጥፋቷ መቃረቡን ዕወቁ።
21. በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በከተማ ያሉትም ከዚያ ይውጡ፤ በገጠር ያሉትም ወደ ከተማዪቱ አይግቡ፤
22. የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይህ የበቀል ጊዜ ነውና።
23. በምድሪቱ ላይ ታላቅ መከራ ይሆናል፤ በዚህም ሕዝብ ላይ ቊጣ ይመጣል፤ ስለዚህ በዚያን ወቅት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ እናቶች ወዮላቸው!