ሉቃስ 20:25-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” ብለው መለሱለት።እርሱም፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው።

26. ስለዚህ በተናገረው ቃል በሕዝቡ ፊት ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም ተገርመው ዝም አሉ።

27. ትንሣኤ ሙታን የለም ከሚሉት ሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ወደ ኢየሱስ መጥተው ጥያቄ አቀረቡለት፤

28. እንዲህም አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ወንድሙ መበለቲቱን አግብቶ ልጆች በመውለድ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል።

29. ታዲያ፣ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤

30. ሁለተኛውም እንደዚሁ፤

31. ሦስተኛው ደግሞ አገባት፤ ሰባቱም እንዲሁ እያሉ አግብተዋት ልጆች ሳይወልዱ ሞቱ።

32. በመጨረሻም ሴትዮዋ ሞተች።

33. እንግዲህ ሰባቱም ስላገቧት፣ በትንሣኤ ጊዜ የማን ሚስት ትሆናለች?”

34. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ፤ ይጋባሉም፤

35. የሚመጣውን ዓለምና የሙታንን ትንሣኤ ማግኘት የሚገባቸው ግን አያገቡም፤ አይጋቡም፤

36. እንደ መላእክትም ስለሆኑ ከዚያ በኋላ አይሞቱም፤ የትንሣኤ ልጆች ስለ ሆኑም የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።

37. ሙሴ ስለ ቊጥቋጦ በተጻፈው ታሪክ ውስጥ ጌታን፣ ‘የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ’ በማለቱ ሙታን እንደሚነሡ ያሳያል፤

38. ሁሉም ለእርሱ ሕያዋን ስለሆኑ፣ እርሱ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አይ ደለም።”

ሉቃስ 20