9. የጌታም መልአክ ድንገት መጥቶ በአጠገባቸው ቆመ፤ የጌታም ክብር በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅም ፍርሀት ያዛቸው።
10. መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች አምጥቼላችኋለሁና።
11. ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀን ተወልዶላችኋልና፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው።
12. ይህ ምልክት ይሁናችሁ፤ ሕፃን ልጅ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ።”
13. ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋር ታዩ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ እንዲህ አሉ፤
14. “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!”
15. መላእክቱ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከወጡ በኋላ እረኞቹ፣ “ጌታ የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንድናይ ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ” ተባባሉ።
16. እነርሱም ፈጥነው ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ።
17. ካዩም በኋላ፣ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን ገልጠው አወሩ።
18. ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤
19. ማርያም ግን ይህንን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር።
20. እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ።