18. ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤
19. ማርያም ግን ይህንን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር።
20. እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ።
21. ስምንት ቀን ሆኖት የመገረዣ ጊዜው ሲደርስ፣ ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስም ኢየሱስ ተባለ።
22. በሙሴ ሕግ መሠረት፣ የመንጻታቸው ወቅት በተፈፀመ ጊዜ፣ ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ወጡ፤
23. ይኸውም በጌታ ሕግ፣ “ተባዕት የሆነ በኵር ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ለመፈጸምና
24. ደግሞም በጌታ ሕግ፣ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፣” መሥዋዕት ለማቅረብ ነበር።
25. በዚያን ጊዜ ጻድቅና ትጒሕ የሆነ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው በኢየሩሳሌም ይኖር ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን መጽናናት የሚጠባበቅና መንፈስ ቅዱስ በላዩ ያደረሰው ነበር።
26. ደግሞም የጌታን መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር፤
27. እርሱም በዚህ ጊዜ በመንፈስ ተመርቶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ የልጁም ወላጆች በሕጉ ልማድ መሠረት ተገቢውን ሊፈጽሙለት ሕፃኑን ኢየሱስን ይዘው በገቡ ጊዜ፣
28. ስምዖን ተቀብሎ ዐቀፈው፤ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲህ አለ፤
29. “ጌታ ሆይ፤ ቃል በገባኸው መሠረት፣አሁን ባሪያህን በሰላም አሰናብተው፤
30. ዐይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን፣
31. ማዳንህን አይተዋልና።
32. ይህም ለአሕዛብ መገለጥን የሚሰጥ ብርሃን፣ለሕዝብህ ለእስራኤልም ክብር ነው።”
33. አባቱና እናቱም ስለ እርሱ በተነገረው ነገር ተገረሙ።
34. ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፤ “ይህ ሕፃን በእስራኤል ለብዙዎች መነሣትና መውደቅ ምክንያት እንዲሆን፣ ደግሞም ክፉ ለሚያስወሩበት ምልክት እንዲሆን ተወስኖአል፤
35. የብዙዎችም የልብ ሐሳብ የተገለጠ እንዲሆን፣ የአንቺም ነፍስ ደግሞ በሰይፍ ይወጋል።”
36. ደግሞም ከአሴር ወገን የሆነች የፋኑኤል ልጅ፣ ሐና የምትባል ነቢይት በዚያ ነበረች፤ እርሷም በጣም አርጅታ ነበር፤ በድንግልናዋ ካገባችው ባሏም ጋር ሰባት ዓመት የኖረች ነበረች፤
37. ዕድሜዋም ሰማንያ አራት ዓመት እስኪሆናት ድረስ ቀንና ሌሊት ከቤተ መቅደስ ሳትለይ፣ በጾምና በጸሎት የምታገለግል መበለት ሆና ቈየች።
38. በዚያኑም ጊዜ ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም መቤዠት ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ሕፃኑ ተናገረች።