ሉቃስ 2:14-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!”

15. መላእክቱ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከወጡ በኋላ እረኞቹ፣ “ጌታ የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንድናይ ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ” ተባባሉ።

16. እነርሱም ፈጥነው ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ።

17. ካዩም በኋላ፣ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን ገልጠው አወሩ።

18. ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤

19. ማርያም ግን ይህንን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር።

20. እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ።

21. ስምንት ቀን ሆኖት የመገረዣ ጊዜው ሲደርስ፣ ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስም ኢየሱስ ተባለ።

22. በሙሴ ሕግ መሠረት፣ የመንጻታቸው ወቅት በተፈፀመ ጊዜ፣ ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ወጡ፤

23. ይኸውም በጌታ ሕግ፣ “ተባዕት የሆነ በኵር ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ለመፈጸምና

24. ደግሞም በጌታ ሕግ፣ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፣” መሥዋዕት ለማቅረብ ነበር።

25. በዚያን ጊዜ ጻድቅና ትጒሕ የሆነ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው በኢየሩሳሌም ይኖር ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን መጽናናት የሚጠባበቅና መንፈስ ቅዱስ በላዩ ያደረሰው ነበር።

26. ደግሞም የጌታን መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር፤

27. እርሱም በዚህ ጊዜ በመንፈስ ተመርቶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ የልጁም ወላጆች በሕጉ ልማድ መሠረት ተገቢውን ሊፈጽሙለት ሕፃኑን ኢየሱስን ይዘው በገቡ ጊዜ፣

28. ስምዖን ተቀብሎ ዐቀፈው፤ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲህ አለ፤

ሉቃስ 2