2. ስሙ ዘኬዎስ የተባለ አንድ ሰው በዚያ ነበረ፤ ዋና ቀረጥ ሰብሳቢና ሀብታም ነበረ።
3. እርሱም ኢየሱስ የተባለው የትኛው እንደሆነ ሊያይ ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱ አጭር ነበረና ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ሊያየው አልቻለም።
4. ኢየሱስ በዚያ መንገድ ያልፍ ስለ ነበርም፣ ሊያየው ወደ ፊት ሮጦ አንድ ሾላ ዛፍ ላይ ወጣ።
5. ኢየሱስም እዚያ ቦታ ሲደርስ፣ ቀና ብሎ፣ “ዘኬዎስ ሆይ፤ ዛሬ አንተ ቤት መዋል ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ” አለው።
6. እርሱም ፈጥኖ ወርዶ በደስታ ተቀበለው።
7. በዚያ የነበሩ ሰዎችም ይህንን አይተው፣ “ከኀጢአተኛ ቤት ገብቶ ሊስተናገድ ነው።” በማለት ሁሉም ማጒረምረም ጀመሩ።
8. ዘኬዎስ ግን ቆመና ጌታን፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆ ካለኝ ሀብት ሁሉ ግማሹን ለድኾች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ቀምቼ ከሆነ፣ አራት ዕጥፍ አድርጌ እመልሳለሁ” አለው።
9. ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “ይህ ሰው ደግሞ የአብርሃም ልጅ ስለ ሆነ፣ ዛሬ መዳን ወደዚህ ቤት መጥቶአል፤
10. ምክንያቱም የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን ነው።”
11. ሕዝቡ ይህን እየሰሙ ሳሉ፣ በምሳሌ መናገሩን ቀጠለ፤ ምክንያቱም ወደ ኢየሩሳሌም በመቃረቡና ሰዎቹም የእግዚአብሔር መንግሥት የሚገለጥ ስለ መሰላቸው ነው።
12. ስለዚህም እንዲህ አለ፤ “አንድ መስፍን የንጉሥነትን ማዕረግ ተቀብሎ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር ሄደ።
13. ከአገልጋዮቹም መካከል ዐሥሩን ጠርቶ ዐሥር ምናን ሰጣቸውና “ተመልሼ እስክመጣ ድረስ በዚህ ገንዘብ ነግዱበት” አላቸው።
14. “የአገሩ ሰዎች ግን ስለ ጠሉት፤ ‘ይህ ሰው በላያችን እንዲነግሥ አንፈልግም’ ብለው ከኋላው መልእክተኞችን ላኩበት።
15. “ይሁን እንጂ ይህ መስፍን ንጉሥ ሆኖ ወደ አገሩ ተመለሰ፤ እነዚያ አገልጋዮቹም እርሱ በሰጣቸው ገንዘብ ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ለማወቅ አስጠራቸው።
16. “የመጀመሪያው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ የሰጠኸኝ ምናን ዐሥር ምናን ትርፍ አስገኝቶአል’ አለው።
17. “ጌታውም፣ ‘አንተ ታማኝ አገልጋይ፣ መልካም አድርገሃል፤ በትንሽ ነገር ታማኝ ሆነህ ስለ ተገኘህ፣ በዐሥር ከተሞች ላይ ሥልጣን ተሰጥቶሃል’ አለው።
18. “ሁለተኛውም ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ የሰጠኸኝ ምናን አምስት ምናን ትርፍ አስገኝቶአል’ አለው።