3. “መጋቢውም በልቡ እንዲህ አለ፤ ‘ጌታዬ ከመጋቢነት ሊሽረኝ ነው፤ ለማረስ ጒልበት የለኝም፤ መለመን ደግሞ ዐፍራለሁ፤ ስለዚህ ምን ላድርግ?
4. ከመጋቢነት የተሻርሁ እንደሆነ ሰዎች በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን ዐውቃለሁ።’
5. “ስለዚህ የጌታው ዕዳ ያለባቸውን ሰዎች እያንዳንዳቸውን ጠራ፤ የመጀመሪያውንም ሰው ‘የጌታዬ ዕዳ ምን ያህል አለብህ?’ አለው።
6. “እርሱም፣ ‘አንድ መቶ ማድጋ ዘይት አለብኝ’ አለ። “መጋቢውም፣ ‘የውል ወረቀትህን እንካ፤ ቶሎ ተቀምጠህ “አምሳ ማድጋ” ብለህ ጻፍ’ አለው።
7. “ከዚያም ሌላውን፣ ‘አንተስ ስንት አለብህ?’ አለው። “እርሱም፣ ‘አምሳ ዳውላ ስንዴ’ አለው። “መጋቢውም፣ ‘የብድር ደብዳቤህን እንካ፤ “አርባ ዳውላ” ብለህ ጻፍ’ አለው።
8. “ጌታውም አጭበርባሪውን መጋቢ በብልኅነቱ አደነቀው፤ የዚህ ዓለም ልጆች ከመሰሎቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ከብርሃን ልጆች ይልቅ ብልኆች ናቸውና።