ሉቃስ 13:20-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር ላመሳስላት?

21. አንዲት ሴት ወስዳ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በዛ ካለ ዱቄት ጋር የደባለቀችውን እርሾ ትመስላለች።”

22. ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ ሳለ፣ በሚያልፍባቸው ከተሞችና መንደሮች እያስተማረ ያልፍ ነበር።

23. አንድ ሰውም ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚድኑት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸውን?” አለው።እርሱም እንዲህ አላቸው፤

24. “በጠባቧ በር ለመግባት ተጣጣሩ፤ እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ለመግባት ይፈልጋሉ ነገር ግን አይሆንላቸውም፤

25. የቤቱ ባለቤት ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ በውጭ ቆማችሁ፣ ጌታ ሆይ፤ ክፈትልን እያላችሁ በሩን ማንኳኳት ትጀምራላችሁ። “እርሱ ግን፣ ‘ማን እንደሆናችሁና ከየት እንደመጣችሁ አላውቅም’ ብሎ ይመልስላችኋል።

26. “እናንተም፣ ከአንተ ጋር አብረን በልተናል፤ ጠጥተናል፤ በአደባባያችንም አስተምረሃል ትላላችሁ።

27. “እርሱም፣ እላችኋለሁ፤ ‘ማን እንደሆናችሁና ከየት እንደመጣችሁ አላውቅም፤ እናንት ዐመፀኞች ሁሉ ከእኔ ራቁ’ ይላል።

28. “አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን፣ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስታዩ፣ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ በዚያን ጊዜ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።

29. ሰዎች ከምሥራቅ፣ ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ መጥተው በእግዚአብሔር መንግሥት በማእድ ይቀመጣሉ።

30. እነሆ፤ ከኋለኞች መካከል ፊተኞች የሚሆኑ፣ ከፊተኞች መካከልም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።”

31. በዚያን ጊዜ ከፈሪሳውያን አንዳንዶች መጥተው፣ “ሄሮድስ ሊገድልህ ስለሚፈልግ ተነሥተህ ከዚህ ሂድ” አሉት።

32. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሄዳችሁ ለዚያ ቀበሮ፣ እነሆ፤ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ፤ ሕመምተኞችን እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ከግቤ እደርሳለሁ ብሎአል በሉት፤

33. ይሁን እንጂ ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ይሞት ዘንድ አይገባምና ዛሬና ነገ፣ ከነገ ወዲያም ወደዚያው ጒዞዬን እቀጥላለሁ።

34. “ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ነቢያትን የምትገድዪ፣ ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ፣ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ፤ እናንተ ግን እምቢ አላችሁ፤

35. እነሆ፤ ቤታችሁ ወና ሆኖ ቀርቶአል። እላችኋለሁ፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ አታዩኝም።”

ሉቃስ 13