ሉቃስ 12:4-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. “ወዳጆቼ ሆይ፤ እላችኋለሁ ሥጋን የሚገድሉትን፣ ከዚያ ወዲያ ግን ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ።

5. ነገር ግን መፍራት የሚገባችሁን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን እርሱን ፍሩት፤ አዎን፤ እርሱን ፍሩት እላችኋለሁ።

6. አምስት ድንቢጦች በዐሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ይሁን እንጂ ከእነርሱ አንዷ እንኳ በእግዚአብሔር ዘንድ አትዘነጋም።

7. የእናንተ የራሳችሁ ጠጒር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላችሁ።

8. “እላችኋለሁ፤ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል።

9. በሰው ፊት የሚክደኝም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል።

10. በሰው ልጅ ላይ የማቃለል ቃል የሚሰነዝር ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ግን አይሰረይለትም።

11. “ሰዎች ይዘው ወደ ምኵራብ፣ ወደ ገዥዎችና ወደ ባለ ሥልጣናት ባቀረቧችሁ ጊዜ፣ እንዴት ወይም ምን እንደምትመልሱ አትጨነቁ፤

12. በዚያ ሰዓት መንፈስ ቅዱስ መናገር የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና።”

13. ከሕዝቡም መካከል አንድ ሰው፣ “መምህር ሆይ፤ ወንድሜ ውርስ እንዲያካፍለኝ ንገረው” አለው።

14. ኢየሱስም፣ “አንተ ሰው፤ በእናንተ ላይ ፈራጅ ወይም ዳኛ ያደረገኝ ማነው?” አለው።

15. ደግሞም፣ “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ ስላልሆነ፣ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግ ብነትም ሁሉ ራሳችሁንም ጠብቁ” አላ ቸው።

16. ቀጥሎም እንዲህ ሲል ምሳሌ ነገራቸው፤ “ዕርሻው እጅግ ፍሬያማ የሆነችለት አንድ ሀብታም ነበረ፤

17. ይህም ሰው፣ ምርቴን የማከማችበት ስፍራ ስለሌለኝ ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ።

18. “እንዲህም አለ፤ ‘እንደዚህ አደርጋለሁ፤ ያሉኝን ጐተራዎች አፈርስና ሌሎች ሰፋ ያሉ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያም ምርቴንና ንብረቴንም ሁሉ አከማቻለሁ፤

19. ነፍሴንም፣ “ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ” እላታለሁ።’

ሉቃስ 12