ሉቃስ 11:38-54 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

38. ፈሪሳዊውም ኢየሱስ ከምግብ በፊት እጁን እንዳልታጠበ ባየ ጊዜ ተደነቀ።

39. ጌታም እንዲህ አለው፤ “አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጫዊ ክፍል ታጸዳላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በስስትና በክፋት የተሞላ ነው።

40. እናንት ሞኞች፤ የውጪውን የፈጠረ የውስጡንም አልፈጠረምን?

41. ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋል።

42. “እናንት ፈሪሳውያን ግን ወዮላችሁ፤ ከአዝሙድና ከጤና አዳም እንዲሁም ከአትክልት ሁሉ ዐሥራት ታወጣላችሁ፤ ሆኖም ፍትሕንና እግዚአብሔርን መውደድ ቸል ትላላችሁ፤ ነገር ግን ያንን ሳትተዉ ይኸኛውን ማድረግ በተገባችሁ ነበር።

43. “እናንት ፈሪሳውያን ወዮላችሁ፤ በምኵራብ የክብር መቀመጫ፣ በገበያ መካከልም እጅ መነሣትን ትወዳላችሁና።

44. “ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበትን የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፣ ወዮላችሁ።”

45. ከሕግ ዐዋቂዎች አንዱ መልሶ “መምህር ሆይ፤ እንዲህ ስትናገር እኮ እኛንም መስደብህ ነው” ሲል መለሰለት።

46. ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “እናንት ሕግ ዐዋቂዎችም ደግሞ ወዮላችሁ፤ ሰዎች ሊሸከሙ የማይችሉትን ከባድ ሸክም ታሸክማላችሁ፤ እናንተ ራሳችሁ ግን በጣታችሁ እንኳ አትነኵትም።

47. “አባቶቻችሁ የገደሏቸውን የነቢያትን መቃብር ስለምታበጃጁ፣ ወዮላችሁ፤

48. እንግዲህ የአባቶቻችሁን ሥራ የምታጸኑ ምስክሮች ናችሁ፤ እነርሱ ነቢያትን ገደሉ፣ እናንተም መቃብራቸውን ታበጃጃላችሁ።

49. ስለዚህም የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች፤ ‘ነቢያትንና ሐዋርያትን እልክላቸዋለሁ፤ እነርሱ አንዳንዶቹን ይገድላሉ፤ ሌሎችንም ያሳድዳሉ።’

50. ስለዚህ ይህ ትውልድ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ስለ ፈሰሰው፣ ስለ ነቢያት ሁሉ ደም ተጠያቂ ነው፤

51. ከአቤል ደም ጀምሮ፣ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ መካከል እስከ ፈሰሰው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ ይፈለግበታል፤ አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ይህ ትውልድ ለዚህ ተጠያቂ ነው።

52. “እናንት ሕግ ዐዋቂዎች ወዮላችሁ፤ የዕውቀትን መክፈቻ ነጥቃችሁ ወስዳችኋልና፤ እናንተ ራሳችሁ አልገባችሁበትም፤ የሚገቡትንም ከልክላችኋል።”

53. ኢየሱስ ከዚያ ከወጣ በኋላ፣ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ክፉኛ ይቃወሙትና በጥያቄም ያዋክቡት ጀመር፤

54. ከአፉ በሚወጣውም ቃል ሊያጠምዱት ያደቡ ነበር።

ሉቃስ 11