ሉቃስ 1:34-51 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

34. ማርያምም መልአኩን፣ “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው።

35. መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።

36. እነሆ፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተ እርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን የተባለችውም ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤

37. ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።”

38. ማርያምም፣ “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቶአት ሄደ።

39. ማርያምም በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤

40. ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች።

41. ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤

42. ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።

43. ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ?

44. እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሎአልና።

45. ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!”

46. ማርያምም እንዲህ አለች፤“ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤

47. መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤

48. እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቶአልና።ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉብፅዕት ይሉኛል፤

49. ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤

50. ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድእስከ ትውልድ ይኖራል።

51. በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቶአል፤በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኖአቸዋል፤

ሉቃስ 1