2 ዜና መዋዕል 7:8-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. በዚያን ጊዜ ሰሎሞን ከእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ጋር ለሰባት ቀን በዓሉን አከበረ፤ ሕዝቡም ከሐማት መግቢያ እስከ ግብፅ ወንዝ ድረስ ካለው ምድር የመጣ እጅግ ታላቅ ጉባኤ ነበር።

9. መሠዊያውን ለሰባት ቀን ስለ ቀደሱና የሰባት ቀን በዓል በተጨማሪ ስላከበሩ፣ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አደረጉ።

10. ሰሎሞንም በሰባተኛው ወር፣ በሃያ ሦስተኛው ቀን ወደየቤታቸው እንዲሄዱ ሕዝቡን አሰናበተ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔር ለዳዊትና ለሰሎሞን እንዲሁም ለሕዝቡ ለእስራኤል ስላደረገው በጎ ነገር ሁሉ በልባቸው ደስ እያላቸውና ሐሤት እያደረጉ ሄዱ።

11. ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥቱን ሥራ ጨረሰ፤ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለራሱ ቤተ መንግሥት ያደርግ ዘንድ በልቡ ያሰበውን ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣

12. እግዚአብሔር በሌሊት ተገልጦለት እንዲህ አለው፤“ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህንንም ስፍራ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቤተ መቅደስ እንዲሆን ለራሴ መርጬዋለሁ።

13. “ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማያትን በምዘጋበት ጊዜ ወይም ምድሪቱን እንዲበላ አንበጣ በማዝበት ጊዜ፣ ወይም በሕዝቤ ላይ ቸነፈር በምሰድበት ጊዜ፣

14. በስሜ የተጠራው ሕዝቤ ራሱን አዋርዶ ቢጸልይ፣ ፊቴን ቢፈልግና ከክፉ መንገዱ ቢመለስ፣ ከሰማይ እሰማዋለሁ፤ ኀጢአቱን ይቅር እላለሁ፤ ምድሩንም እፈውሳለሁ።

15. አሁንም በዚህ ስፍራ ወደሚጸለየው ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮዎቼም ያዳምጣሉ።

16. ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤተ መቅደስ መርጫለሁ፤ ቀድሸዋለሁም። ዓይኖቼም ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።

17. “አንተም ደግሞ አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በፊቴ ብትሄድ፣ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትፈጽም፣ ሥርዐቶቼንና ሕግጋቴን ብትጠብቅ፣

18. ለአባትህ ለዳዊት፣ ‘ከዘርህ እስራኤልን የሚገዛ አታጣም’ ብዬ በገባሁለት ቃል ኪዳን መሠረት የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ።

2 ዜና መዋዕል 7