1. ኢዮስያስ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ፋሲካን አደረገ፤ በመጀመሪያውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካው በግ ታረደ።
2. ካህናቱን በየአገልግሎታቸው መደበ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎትም እንዲተጉ አበረታታቸው።
3. እስራኤልን ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩትና ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አላቸው፤ “የእግዚአብሔርን ታቦት የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ባሠራው ቤተ መቅደስ አኑሩ፤ በእናንተ ትከሻ አትሸከሙት፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ።
4. በእስራኤል ንጉሥ በዳዊትና በልጁ በሰሎሞን በተጻፈው መመሪያ መሠረት፣ እንደየቤተሰባችሁ በክፍል በክፍላችሁ ራሳችሁን አዘጋጁ።
5. “ሌዋውያን ባልሆኑ ወንድሞቻችሁ አንጻር እንደየቤተ ሰቡ ምድብ በተቀደሰው ስፍራ ቁሙ፤ ለእያንዳንዱም የቤተ ሰብ ምድብ ሌዋውያን ይኑሩት።
6. ከዚያም የፋሲካውን በጎች እረዱ፤ ራሳችሁን ቀድሱ፤ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ባዘዘውም መሠረት ዕርዶቹን ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።”