1. ምናሴ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አምሳ አምስት ዓመት ገዛ።
2. እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳዶ ያስወጣቸውን ሕዝቦች አስጸያፊ ልማድ በመከተልም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።
3. አባቱ ሕዝቅያስ ያጠፋቸውን የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች መልሶ ሠራ፤ ለበአሊም መሠዊያዎችን አቆመ፤ የአሼራንም ዐምዶች ሠራ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊትም ሰገደ፤ አመለካቸውም።
4. እግዚአብሔር፣ “ስሜ ለዘላለም በኢየሩሳሌም ይኖራል” ባለበት በእግዚአብሔር ቤተ መቀደስ መሠዊያዎችን ሠራ።
5. በሁለቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ላይ፣ ለሁሉም የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት መሠዊያዎችን ሠራ።
6. በሄኖም ልጅ ሸለቆ ወንዶች ልጆቹን በእሳት ሠዋ፤ አስማት፣ መተትና ጥንቈላ አደረገ፤ ሙታን ጠሪዎችንና መናፍስት ሳቢዎችን ጠየቀ። ለቊጣ ያነሣሣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።