2 ዜና መዋዕል 29:10-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. አሁንም አስፈሪ ቊጣው ከእኛ እንዲመለስ፣ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት አስቤአለሁ።

11. ልጆቼ ሆይ፤ እንግዲህ ቸል አትበሉ፤ በፊቱ እንድትቆሙና እንድታገለግሉት፣ በፊቱም አገልጋዮቹ እንድትሆኑና ዕጣን እንድ ታጥኑለት እግዚአብሔር መርጦአችኋልና።”

12. ከዚያም እነዚሁ ሌዋውያን በሥራው ላይ ተሰማሩ፤ ከቀዓት ዘሮች የአማሢ ልጅ መሐትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮኤል፤ከሜራሪ ዘሮች፣የአብዲ ልጅ ቂስና የይሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፤ከጌድሶን ዘሮች፣የዛማት ልጅ ዮአክና የዮአክ ልጅ ዔድን፤

13. ከኤሊጻፋን ዘሮች፣ሺምሪና ይዒኤል፤ከአሳፍ ዘሮች፣ዘካርያስና መታንያ፤

14. ከኤማን ዘሮች፣ይሒኤልና ሰሜኢ፣ከኤዶታም ዘሮች፣ሸማያና ዑዝኤል።

15. ወንድሞቻቸውን ከሰበሰቡና ራሳቸውን ከቀደሱ በኋላ፣ ንጉሡ የእግዚአብሔርን ቃል ተከትሎ ባዘዘው መሠረት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማንጻት ገቡ።

16. ካህናቱ የእግዚአብሔርን መቅደስ ለማንጻት ወደ ውስጡ ገቡ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገኙትንም ማናቸውንም የረከሰ ነገር ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ አወጡት። ሌዋውያኑም ተሸክመው በመውሰድ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ ጣሉት።

17. ማንጻቱንም በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን ጀምረው በዚያኑ ወር በስምንተኛው ቀን እስከ መቅደስ ሰበሰብ ደረሱ፤ በሚቀጥሉትም ስምንት ቀናት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቀደሱ፤ የመቀደሱም ሥራ በመጀመሪያው ወር በዐሥራ ስድስተኛው ቀን ተጠናቀቀ።

18. ከዚያም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው እንዲህ አሉ፤ “የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሙሉ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ከነዕቃዎቹ ሁሉ፣ ኀብስተ ገጹ የሚቀመጥበትን ጠረጴዛ፣ ከነዕቃዎቹ አንጽተናል።

19. ንጉሥ አካዝ ነግሦ ሳለ ታማኝነቱን ትቶ፣ ከቦታቸው ያነሣቸውን ዕቃዎች ሁሉ አዘጋጅተን ቀድሰናቸዋል፤ እነሆ፤ ዕቃዎቹ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠዊያ ፊት ለፊት ናቸው።”

20. በማግስቱም ጧት በማለዳ፣ ንጉሥ ሕዝቅያስ የከተማዪቱን ሹማምት በአንድነት ሰብስቦ፣ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጣ፤

21. እነርሱም ስለ መንግሥቱ፣ ስለ መቅደሱና ስለ ይሁዳ ሰባት ወይፈኖች፣ ሰባት አውራ በጎች፣ ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ሰባት ተባዕት የፍየል ጠቦቶች ለኀጢአት መሥዋዕት አቀረቧቸው፤ ንጉሡም እነዚህን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ እንዲያቀርቡ የአሮንን ዘሮች ካህናቱን አዘዘ።

22. ካህናቱም ወይፈኖቹን ዐርደው ደሙን በመውሰድ በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም ዐርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ እንደዚሁም ጠቦቶቹን ዐርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩት።

23. ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆኑትን ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፤ እነርሱም እጆቻቸውን ጫኑባቸው።

24. ንጉሡ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት ስለ እስራኤል ሁሉ እንዲቀርብ አዞ ስለ ነበር፣ ካህናቱ ፍየሎቹን ዐርደው ስለ እስራኤል ሁሉ ማስተስረያ እንዲሆን የኀጢአት መሥዋዕት በማድረግ ደሙን በመሠዊያው ላይ አቀረቡ።

2 ዜና መዋዕል 29