1. ከዚህ በኋላ የይሁዳ ሕዝብ በሙሉ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፈንታ አነገሡት።
2. አሜስያስ እንደ አባቶቹ ሁሉ ካንቀላፋ በኋላ፣ ኤላትን እንደ ገና የሠራት፣ ወደ ይሁዳም የመለሳት ዖዝያን ነበር።
3. ዖዝያን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ አምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
4. እርሱም አባቱ አሜስያስ እንደ አደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
5. እግዚአብሔርን መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርን በፈለገ መጠንም አምላክ ነገሮችን አከናወነለት።
6. በፍልስጥኤማውያን ላይ ዘምቶ የጌትን፣ የየብናንና የአዛጦንን ቅጥሮች አፈረሰ። ከዚያም በአዛጦን አጠገብና በቀሩትም የፍልስጥኤም ግዛቶች ውስጥ ከተሞችን እንደ ገና ሠራ።
7. እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን፣ በጉርበኣል በሚኖሩ ዐረቦችና በምዑናውያን ላይ ድልን አቀዳጀው።
8. አሞናውያን ለዖዝያን ግብር ገበሩለት፤ ኀይሉ ስለ ገነነም ዝናው እስከ ግብፅ ዳርቻ ወጣ።
9. ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማዕዘኑ በር፣ በሸለቆው በርና በቅጥሩ ማዕዘን ማማዎች ሠርቶ መሸጋቸው።
10. እንዲሁም በየኰረብታው ግርጌና በየሜዳው ላይ ብዙ የቀንድ ከብት ስለ ነበረው፣ በምድረ በዳ የግንብ ማማዎች ሠራ፤ ብዙ የውሃ ጒድጓዶችም ቈፈረ። ግብርና ይወድ ስለ ነበረም በኰረብታዎችና ለም በሆኑ መሬቶች ላይ ዕርሻ የሚያርሱና ወይን የሚተክሉ ሰራተኞች ነበሩት።